
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ወለድ 102ኛ ክፍለ ጦር በሰሜን ዕዝ ላይ የህገወጡ ትህነግ ልዩ ሃይል የፈጸመው ጥቃት በእጅጉ አሳፋሪ፣ ሃገራዊ ክህደትና በወታደራዊ ሕግ የሚያስጠይቅ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ገልጿል።
ጦሩ በመግለጫው እንዳለው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ነፃነታቸውን አስጠብቀው ከኖሩ ጥቂት ሃገራት አንዷና እንደነፃነት ቀንዲል የምትታይ የመላው ጥቁር ሕዝብ መመኪያ ናት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራትም ሆነ ከአውሮፓውያን በተለያየ ጊዜ የተቃጣባትን ጥቃት መክታ መመለስ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሃገራትን ሰላም ለማስጠበቅ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ዘምቶ ታሪክ የሚያወሳው ጀብድ ፈጽሟል።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የህገወጡ የትህነግ ልዩ ሃይል የፈጸመው ጥቃት በእጅጉ አሳፋሪ፣ ሃገራዊ ክህደትና በወታደራዊ ሕግ የሚያስጠይቅ ከፍተኛ ወንጀል ሆኖ አግኝተነዋል ብሏል፤ይህንን ከጀርባ የተፈጸመ አስነዋሪ ደባ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ወለድ 102ኛ ክፍለ ጦር አባላት አምርረን እንደምናወግዘው እየገለጽን ትናንት ለሉዓላዊነቷ ለደማንላት ውድ ሃገራችን ዛሬም በግንባር ቀደምትነት እንደምንቆም ለመላው ሕዝባችን እንገልጻለን ሲል ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።