
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም (አብመድ) ህገወጡንና ዘራፊውን የትህነግ ቡድን ለመመከት ከሀገር መከላከያ እና ከአማራ ልዩ ሀይል ጎን በመሰለፍ ሙሉ የትጥቅና የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ ወደ መከላከል መግባታቸውን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ግንባር የገቡ የሚሊሻ አባላት ተናግረዋል።
ከጎንደር፣ ከቆላድባ፣ ከጠገዴ፣ ከሶሮቃና ከሌሎች አካባቢዎች የተወጣጡ የሚሊሻ አባላት ናቸው ሙሉ የትጥቅና የሥነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ ወደ መከላከል ተግባር መግባታቸውን የገለጹት፡፡ የሚሊሻ አባላቱ ጥቃት በተሰነዘረበት አካባቢ በመድረስ አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ዘራፊውና ጠብ አጫሪው የህወሃት ቡድን ህዝቦችን ለእንግልትና ለመከራ ሲዳርግ የነበረው ሳያንስ ለሀገር ሉዓላዊነት ሲል ራሱን አሳልፎ እየሰጠ ባለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት መፈጸሙ እንዳበሳጫቸውም ተናግረዋል፡፡
‹‹ሁሉም የትግራይ ህዝብ ወንድምና እህታችን ነው›› ያሉት የሚሊሻ አባላቱ በውስጣቸው ያለውን ህገወጥ የህወሃት ጁንታ አናውቅህም በማለት ከትግላችን ጎን ሊሰለፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ጁንታው ራሱን ለፌደራል መንግስትና ለጸጥታ ሀይሎች አሳልፎ እስካልሰጠ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ሰለሞን አንዳርጌ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ