
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እየተወሰደ ያለው እርምጃ የክልሉን ህዝብ ደኅንነት በማይጎዳ መንገድ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከሚወዳት ኢትዮጵያና ኢትየጵያዊያን ወገኖቹ ለመነጠል ሲሰራ የኖረ ድርጅት ነው ያሉት ተወላጆቹ መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ርምጃ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ህወሃት ሲፈጽም የኖራቸው ዘግናኝ ድርጊቶችም ከትግራይ ህዝብ እሴት ያፈነገጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ህገወጡ የህወሃት ቡድን ጥቂቶችን መጠቀሚያ ካደረገው ስርዓት የትግራይ ህዝብ የሚላቀቅበት ወቅት በመሆኑ የህግ ማስከበሩን ስራ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተወላጆቹ በህወሃት ላይ እተወሰደ ያለው ርምጃ ሰላማዊውን ህዝብ የሚጎዳ እንዳይሆን መንግስት ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የአለም ዓቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ህወሃት ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካደረሰና የሀገርን ሀብት ከመዘበረ በኋላ በትግራይ ህዝብ የመደበቅ ሴራ ሰርቷል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ የትግራይን ህዝብና የሀገር ዳር ድንበርን እየጠበቀ ባለበት ወቅት በህወሃት የተፈጸመበት ክህደት ከምንም በላይ የትግራይን ህዝብ ያሳዘነ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ከሃዲው የሕወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ በፈፀመው ጥቃት መንግስት የሚወስደው ርምጃ የትግራይን ህዝብ ነጻነት የማረጋገጥና ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ አላማ እንዳለውም ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አስገንዝበዋል፡፡
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ ለዓመታት የጨቆነውንና በስሙ የነገደበትን የህወሀት ቡድን በህብረት ከትክሻው የሚያወርደበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ- ከአዲስ አበባ