
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም (አብመድ) አባላቱ “ጸረ-ህዝቡ የህውሃት ቡድን ለጥፋት ሊያውላቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ባይደመሰሱ ኖሮ፤ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችል ነበር” ብለዋል።
የቀድሞ የሰራዊቱ አባላት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሃገርን ክብርና አንድነት ለመጠበቅ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልና መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ያገለገሉት ኮሎኔል ተፈራ እሸቴ የኢትዮጰያ ሰራዊት ከሃገር አልፎ በአፍሪካ አህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ስምና ዝና እንዳለው ጠቅሰዋል።
እንደ ኮሎኔል ተፈራ ገለጻ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ለስልጣን ጥማቱ ሲል መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ ከሃገር ክህደት በላይ ነው።
“ድርጊቱ ኢትዮጵያውንን በእጅጉ ያስቆጣ ነው” ብለዋል።
በአገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ትምህርት ቤት በአሰልጣኝነትና በአስተዳደር ፋይናንስ ኃላፊነት እስከ 2002 ዓ.ም ያገለገሉት ሻለቃ ወንዱ ወልዴ በበኩላቸው “ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት ጸረ-ህዝብና ጸረ- አገር መሆኑን ያሳየ ነው” ብለዋል።
ጸረ-ሰላም ቡድኑ የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት ከፍራቻ በመቁጠር የኢትዮጵያ መከታ በሆነው ሰራዊትላይ ጥቃት ፈፅሟል፤ ድርጊቱም በይቅርታ መታለፍ የለበትም ብለዋል።
የቀድሞ ሰራዊት አባላት የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ኃይሎችን ለመመከት ወደ ኋላ እንደማይሉም ተናግረዋል፤ ለዚህ ደግሞ እነሱም ሆኑ ሌሎች ጓዶቻቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን ልማት የማይፈልጉ የውስጥም የውጭም ኃይሎች እኩይ ተግባራቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝቡ አንድነቱን ማጠናከርና አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።