
ባሕር ዳር፡ጥቅምት 27/ 2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ ህወሓት ትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ አስታውቀዋል፡፡
እየተካሄደ ያለው ዘመቻም በሃገሪቱ ህግና ስርአትን ለማስፈን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማስከበር ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ህግና ስርዓት የማስከበሩ ተግባር በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለወራት ታግሶ ድርድርና ሽምግልና ሲያካሂድ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም መንግስት ያደረገው ጥረት በሙሉ በህወሃት እምቢተኝነት መክሸፉንም አስታውቀዋል፡፡