
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጸጥታ አካሉ ህግን የማስከበር ሥራ በሚሰራበት ወቅት ሊያጋጥም የሚችልን የደም እጥረት ለማስቀረት በደም ልገሳው መሳተፋቸውን የምእራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ደም ልገሳውን አጠናክሮ በመቀጠል አንድም የጸጥታ አስከባሪ አካል በደም እጥረት ህይወቱን እንዳያጣ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ለቀጣይ ሁለት ቀናት የደም ልገሳ መርሃግብሩ እንደሚቀጥል የመተማ ደም ባንክ ኃላፊ ወንድሙ አሰፋ ተናግረዋል። ከነዋሪው አራት ሽህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና እስካሁን ከ50 ዩኒት ደም በላይ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጊዜያት በበለጠ በደም ልገሳ ፕሮግራሙ እየተሳተፈ በመሆኑ የታቀደውን የደም መጠን ለመሰብሰብ እንደሚረዳም ኃላፊው መናገራቸውን ባልደረባችን ዳንኤል ወርቄ ከገንዳ ውሃ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ‹‹ደም በመለገስ ክቡር የሆነውን የሠው ልጅ ህይወት እንታደግ›› በሚል መሪ መልእክት በሁሉም ከተሞች የደም ልገሳ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው ፡፡
መርሃግብሩ ከሚካሄድባቸው ከተሞች አንዷ በሆነቸው ኮምቦልቻ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው። የደም ልገሳው ለሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ለሚሊሻ አባላት በፈቃደኝነት የሚለገስ መሆኑንም ዘጋቢያችን ደጀን አምባቸው ተመልክቷል፡፡