
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወቅታዊውን የሃገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው ህወሃት ህዝብ እና ሃገርን ለጥበቃ በተሰማራ የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ላይ ጥቃት መፈፀም ክህደት ነው ብለዋል፡፡ “ጥቃቱን ታሪክ፣ ህግ እና ህሊና ይቅር የማይለው ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል በሚገኙ 22 ትልልቅ የህዝብ እና የመንግስት ተቋማት ላይ የፌደራል ፖሊስ ተልዕኮ ተሰጥቶት ጥበቃ ያካሂድ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ ህወሃት በርካታ ኃይል በመመደብ በአባሎቻችን ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ አሁን ላይ ከጥቃት ወጥቶ በቅንጅት ወደማጥቃት ተመልሷልም ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
የትግራይ ህዝብ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል እና የመንግስት አገልግሎት እንዳይቋረጥ የፌደራል ፖሊስ ህግ የማስከበር ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በትግራይ ክልል ትልልቅ የመንግስት እና የህዝብ ተቋማት ላይ የፌደራል ፖሊስ ተልዕኮ ተሰጥቶት ጥበቃ እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለፁት ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው አሁን ደግሞ በሃገሪቱ ትልልቅ ከተሞች ጥፋት እንዲፈፀም ኃይል መሰማራቱ ተደርሶበታል ነው ያሉት፡፡ ጥቃት እንደሚፈፀም ከህዝብ ከደረሰ 1 ሺህ 500 በላይ ጥቆማ ውስጥ በርካቶቹ ትክክለኛ መሆናቸው ተረጋግጧል፤ በርካቶቹን በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ የምርመራ ስራ መጀመሩን እና በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ የክትትል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ህዝቡም መንግስት የሚሰጠውን መልዕክት እየተከታተለ ተልዕኮውን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን – ከአዲስ አበባ