የሕዝብ ሠላምን በአስተማማኝ መልኩ ማስቀጠል የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠሩን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፤ በዞኑ የጸጥታ ችግር የስጋት ቀጣና በተባሉ አካባቢዎች ጠንካራ አመራር እየተሠጠ መሆኑን የዞኑ የሕዝብ ሠላምና ደኅነት መምሪያ ገልጿል፡፡

194

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቶት በተሰማራው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ በከሃዲው ትህነግ የተፈጸመው ጥቃት እንዳሳዘነው መምሪያው አመላክቷል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አበራ መኮንን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው የህወሃት(ትህነግ) እኩይ ተግባር ሀገርን የመበታተን ዓላማ ይዞ መሆኑን ተናግረዋል፤ በዞኑ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

ኦነግ ሸኔ በዞኑ ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ እንደሚያደርግ የገለፁት ኃላፊው የጥፋት ሃይሉ ሙከራ በተግባር እንዳልተሳካለትም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኃላፊው መረጃ የጸጥታ ስጋት ይኖርባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የጥፋት እንቅስቃሴውን በአስተማማኝ ሁኔታ መቀልበስ የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሯል፤ ከአዋሳኝ ወረዳዎችና ዞኖች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠርም ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ አካላዊና ስነልቦናዊ ዝግጅት አድርጓል፤ ከሕዝቡ ጋርም ጥሩ አደረጃጀት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የጸጥታ ስጋቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለማስቀረት በአዋሳኝ አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ፣ በሁሉም አካባቢዎችና አገልግሎት ሰጪ ቋማትም ድንገተኛ ፍተሻ እየተደረገ እንደሚገኝም መምሪያ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ወዲያውኑ ለጸጥታ አካላት እንዲጠቁም የማንቃት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው ማኅበረሰቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ዞኑ ከበፊቱም በጸጥታ ጉዳይ ላይ በልዩ ትኩረት ሲሠራ ቆይቷል፤ ውጤታማ መሆንም ችሏል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሀገር ለማተራመስ የተነሱ አካላት ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግር ለመቀልበስ የቀውስ ጊዜ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የጥፋት ኃይል እንቅስቃሴ ሊኖር የሚችልባቸው ቦታዎችም ተለይተዋል፡፡ በተለዩት አካባቢዎች መከናወን በሚገባቸው ሥራዎች ላይም ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ውይይት ተደርጓል›› ብለዋል፡፡

ሠላምን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት የዞኑን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous article“ደማችን ለመከላከያችን እና ለልዩ ኃይላችን” በሚል መሪ ሃሳብ በደብረ ታቦር ከተማ የደም ልገሳ ፕሮግራም ልገሳ እየተካሄደ ነው።
Next articleበሰሜን ኢትዮጵያ በመከላከያ ሰራዊት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግልጽ፣ የተወሰነ እና ሊደረስበት የሚችል አላማን ያነገበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡