
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በቅርቡ የህወሃት አምባገነን ቡድን በሰሜን እዝ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል፤ ቡድኑን ለመመከት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙት የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት የመቁሰል አደጋ እና የደም እጦት ለሚያጋጥማቸው የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፣ ወጣቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ደም እየለገሱ ናቸው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለም ወርቅ ምህረቴ በሃገራችን ላይ የተቃጣውን ትንኮሳ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት ትንኮሳውን በመከላከል ላይ ናቸው፤ በዚህ ወቅት የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለመቅረፍ ደም እየለገሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ህብረተሰብ በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ አለበት ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ደም መለገስ፣ የምግብ አቅርቦት በማቅረብ እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመደገፍ ህብረተሰቡ የሰራዊቱ ደጀን መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
‹‹ህዝባዊ ደጀን ያለው ስራዊት ተሸንፎ አያውቅም፤ ይህን ወቅት በድል ከተወጣነውም ሃገራችንም ሰላም ትሆናለች ፤ የህዳሴያችንን ጉዞ እናረጋግጣለን›› ብለዋል አስተዳዳሪው ። ዞኑን ሰላም ለማድረግ ስምሪት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ቀለመወርቅ አሁን ላይ ዞኑን የሚያሰጋ ሁኔታ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
የሚሊሻ አባላት ፣ ተጠባባቂ ኃይል እና ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በማደራጀት ጥሪ ሲደረግላቸው ሰራዊቱን እንዲያግዙ የቅደመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከወረዳ እስከ ዞን ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚሆን የቀሳቁስ አቅርቦት ለማድረግ የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው አስታዉቀዋል።
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አግማሴ ገበየሁ በበኩላቸው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ፣የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና የሚሊሻ አባላት መስዋዕትነት እየከፈሉ በመሆናቸው በጦርነት ውስጥ የደም መፍሰስ አደጋ ሊያጋጥም ስለሚችል የሰራዊቱን ህይወት ለመታደግ ደም እየለገሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሃዲው ህውሃት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ከ27 አመታት በላይ ጭቆና ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት አቶ አግማሴ የክልሉ ህዝብ ደም ከመለገስ ባሻገር አንድነቱን አጠናክሮ የቁሳቁስ እና የምግብ አቅርቦት በማቅረብ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ አምባገነኑን ቡድን ማስወገድ እንዳለበትም ገልፀዋል።
በደም ልገሳው እየተሳተፉ የሚገኙ ነዋሪዎች እና ወጣቶችም የመከላከያ ኃይሉን ለማገዝ እና ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ደም እየለገሱ መሆናቸውን ገልፀው በአካባቢያቸው የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም የገንዘብ ፣ የቁሳቁስ እና የጉልበት ድጋፍ በማድረግ በየጊዜው ጥቃት የሚደርስበትን የአማራ ህዝብ ለመታደግ ጊዜው አሁን መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ – ከደብረ ታቦር