
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ ዱቦና ድግኖ ፓርቲ፣ የምዕራብ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ የብልፅግና ፓርቲ እና የእኩልነትና የነጻነት ፓርቲ በጅግጅጋ ከተማ ባደረጉት ስብሰባ ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ተወያይተው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸውም ከሃዲው ህወሃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳፋሪ፣ የሚወገዝና መታለፍ የሌለበት ተግባር ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግስትና የሀገር መከላከያ ኃይላችን በፅንፈኛውና ከሃዲው ህወሃት ላይ እየወሰደ ያለውን ተመጣጣኝና ተገቢ እርምጃን እነደሚደግፉ የገለፁት ፓርቲዎቹ የፌዴራል መንግስት የህወሓትን አገዛዝ ማስወገድ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይም በሶማሌ ህዝብ ላይ ለ27 ዓመታት በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት በመፈፀም በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን የሶማሌ አርብቶ አደር ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ አድርሷል ያሉት ፓርቲዎቹ የፌዴራል መንግስት ይህንን ያደረሱ የህወሓት ቡድን አባላት ለህግ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋና ሰላምና ደህንነቱ እንዲጠበቅ ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር ጎን በመቆም ሙሉ ትብብር እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ህዝብ በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችን በሰላምና በፍቅር፣ የአብሮነት መኖር ባሻገር ወንድማማችነትና መልካም ጉርብትናን እንዲጠብቅም ፓርቲዎቹ በጋራ የአቋም መግለጫቸው መግለፃቸውን ኢብኮ ዘግቧል፡፡