
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በተደጋጋሚ እንደሚባለው “በዓለም ላይ መጥፎ የሚባል ሠላም፤ መልካም የሚባል ጦርነት የለም” በተለይ በትናንትናው አብሮነት መፃዒውም በጋራ በተሳሰረ ወንድም ሕዝብ መካከል የሚፈጠር ግጭት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ካለመኖሩ ሌላ ውጤቱ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ ሠላም ግን ስለተዘመረለት እና ሕዝብ ስለሚፈልግው ብቻ አይመጣም፡፡ ሠላም የሕዝቦችን መሻት ብቻ ሳይሆን የመሪዎችን ይሁንታም ይፈልጋል፡፡ በአንፃሩ ግጭት የሰውን ልጅ ህይዎት የሚቀጥፍ እና ንብረት የሚያወድም ቢሆንም ቅሉ ዛሬም ድረስ ከሰው ልጆች መስተጋብር ሲፋቅ አይስተዋልም፡፡
አሁናዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አስመልክቶ አብመድ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ኮሌጅ የሰብዓዊ መብትና ፌዴራሊዝም መምህር እና ተመራማሪው ሲሳይ መንገስቴ (ዶክተር) ሂደቱን ‹‹የፌዴራል መንግስት ተገዶ የገባበት ህግ የማስከበር እርምጃ›› ብለውታል፡፡ “ግጭት ጠማቂዎቹም ሕዝባዊ ለውጡ ዳር የገፋቸው ጥቂት የቀድሞ አድራጊ ፈጣሪ እና ‘ተገፋን’ ብለው የሚያስቡ ግበረ አበሮቻቸው እንጂ የሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የለውም” ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ፡፡
የመንግስትን ህግ የማስከበር እርምጃ በማኅበራዊ ሚዲያው እና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ሳይቀር የእርስ በርስ ጦርነት አድርጎ ማቅረብ እንደሚስተዋል ዶክተር ሲሳይ ጠቅሰዋል፤ ምክንያቱን ደግሞ “ግጭት ፈጣሪዎቹ የሚፈልጉት የስነ ልቦና ጦርነት ነው” ብለውታል፡፡ በተለይም የትግራይን ሕዝብ በግጭቱ ተሳታፊ ለማድረግ እና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ለመሳብ የታለመ መሆኑን በመጠቆም፡፡
“የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሠላምን አጥብቆ የሚሻ፣ በሃገሩ የሚኮራ፣ እኩል ተጠቃሚነትን የሚፈልግ እና ሃገሩን ከሌሎቹ ወንድም ሕዝቦች ጋር ከጥቃት የሚከላከል ” ሲሉ ገልጸውታል ተመራማሪው፤ “ህግ በማስከበሩ ሂደት በሕዝቦች መካከል የሻከረ የታሪክ ግንኙነት መፈጠር የለበትም” ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ባለፈው ስርዓት የተዛባ ትርክት እና የውሸት ታሪክ በየቦታው እየተሳደደ ሲገደል፣ ሲፈናቀል እና ንብረቱ ሲወድም ቅሬታው ከስርዓት እና ስርዓት አራማጆች ጋር እንጂ ከሕዝብ ጋር ሆኖ እንደማያውቅም አስረድተዋል፡፡ ግጭት ፈላጊዎቹ ቡድኖች አደራጅተው ወደተኩስ ልውውጡ ያሰማሯቸው አብዛኞቹ የልዩ ኃይል አባላት ተገደው እንጂ ጦርነት ፈላጊዎች እንዳይደሉም ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል፤ የአማራ ሕዝብ እያሳየ ያለው ተቀባይነትም ኢትዮጵያዊ አቃፊነቱን እና አስተዋይነቱን ያስመሰከረ እንደሆነ በመጥቀስ፡፡
ህግ የማስከበሩ ሂደት ትኩረቱ “በትግራይ ክልል ከመሸጉ ህገ ወጥ ቡድኖች”ጋር እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አለመሆኑን ኢትዮጵያዊያን መረዳት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፤ “የትግራይ ሕዝብም ከሂደቱ ራሱን ነፃ ሊያወጣ ይገባል” ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ፡፡ ህግ የማስከበሩ እርምጃ የሕዝብን ስሜት የማይጎዳ እና ፍላጎትን የማይፃረር መሆን አለበት ብለዋል፡፡ “ህግ በማስከበሩ ሂደት በሕዝቦች መካከል የሻከረ የታሪክ ግንኙነት መፈጠር የለበትም” ነው ያሉት፤ መንግሰትም በተቻለ መጠን ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት እየፈጠረ እና ትኩረቱን በህገ ወጥ ቡድኑ ላይ ብቻ አነጣጥሮ እርምጃውን መቀጠል እንደሚኖርበትም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ምስል:-ከድረ ገጽ