
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከሀዲው የህወሀት ቡድን ባለፉት 27 አመታት በክልሉና በሀገሪቱ ህዝብ ላይ ሲያደርሰው ከነበረው አስከፊ ጉዳት ባለፉት ሶስት አመታት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን ለውጥ ለማደናቀፍ በተለያየ የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ ተናግረዋል።
መንግስት የአጥፊዎችን እኩይ ሴራ በሆደ ሰፊነት ሲያልፍ መቆየቱን የጠቆሙት አፈጉባኤው ህወሃት ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት መንግስት በሀገር አፍራሹ ህወሃት ላይ እርምጃ እንዲወስድ እንዳስገደደው ተናግረዋል።
መላው የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማገሌዎች የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ መንግስት እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንዲደግፉና የሀገሪቱንና የክልሉን ሰላም ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ አፈ ጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ወቅቱ የክልሉ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር፣ በክልሉ ከሚኖሩና ከክልሉ አዋሳኝ ክልል ህዝቦች ጋር ሰላማዊ አብሮነታቸውን በማጠናከር የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ የሚሰራበት ወቅት በመሆኑ የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች አስተዋፆአቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሀገር ሽማግሌዎች ህወሃት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት መቼም ታሪክ የማይረሳው የሀገር ክህደት መሆኑን ጠቁመው መንግስት በአጥፊው ቡድን ላይ እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ከመንግስት ጎን ሆነው የሀገርና የክልሉን ሰላም አጠናክረው ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ማረጋገጣቸውን የሶማሌ ቴሌሺዥን ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል።