‹‹ሕዝቡ የወቅቱን ፈታኝ ሁኔታ በጥበብ ሊያልፈው ይገባል›› አቶ ሲሳይ ዳምጤ

320

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) መላው የአማራ ክልል ሕዝብ ወቅቱን በልዩ ጥንቃቄ ሊያልፈው እንደሚገባ የክልሉ ሰላምና ደሕንነት ቢሮ አሳስቧል፡፡ በሌሎች ክልሎች በሚኖሩ የአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መላው የአማራ ሕዝቦችን ያስቆጣ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያዩ መሆኑን አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡

ብሔር ተኮር ጥቃቶቹን የፌዴራል መንግሥቱ እየተከታተለ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ችግሩ በተስተዋለባቸው አካባቢዎችም አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በሚኖሩ አማራዎች ላይ የተፈጸመው ብሔር ተኮር ግድያ በጣም የሚያሳፍርና ክልሉን ያሳዘነ አረመኔያዊ ተግባር መሆኑን አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብም ስሜቱን አምርሮ የገለጸበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፤ በተለይ በከተሞች ድርጊቱን በማውገዝ ስሜታቸውን በሰልፍ ለመግለጽ ፍላጎት እንደነበርም አብራርተዋል፡፡ ‹ቢሆን ደስ ባለን ነበር› ያሉት አቶ ሲሳይ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ታሳቢ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

አማራን በጠላትነት ፈርጆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥቃት ለማድረስ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስም እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ተልዕኮውን ለማሳካት ምቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክተዋል፤ በመሆኑም ነገሮችን ሰከን ብሎ ማየት እና ፈታኙን ጊዜ በጥበብ ማለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በልዩ ልዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አማራዎች በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶችን ለመከላከል የአማራ ክልል መንግሥት ከፌዴራል ከክልሉ መንግሥት ጋር የተናበበ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፤መልካም ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፤ በዚህም ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ተችሏል፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን የፌዴራል መንግሥቱ እየተከታተለው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኦነግ ሸኔ ዘር ተኮር ጥቃት እያደረሰ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት በጽንፈኛው ቡድን ላይ ርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleየግብረሃይሉ ሰብሳቢ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም መሆኑን ጠቁመው “ግብረሃይሉም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይሆናል” ብለዋል።
Next articleከኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ