
በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመውና የሚያስተገብረው ግብረሃይል፣ ፖሊስ ወይንም ሌላ ማንኛውንም የጸጥታ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ የማዘዝ ስልጣን እንደተሰጠው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርና የአፈጻጸም ወሰን ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው አዋጁ የሚጸናበትን ጊዜ፣ የአፈጻጸም ወሰንና አዋጁን በሚያስተገብረውና በሚያስፈጽመው ግብረሃይል ስልጣንና ተግባር ላይ ገለጻ አድርገዋል።
አዋጁን የማስፈጸምና የማስተግበር ስልጣን የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሃይል መሆኑንም ተናግረዋል።
የአዋጁ የአፈጻጸም ወሰን በዋናነት በትግራይ ክልል ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ግብረሃይሉ ሊያሰፋውና ሊያጠበው እንደሚችልም ዶክተር ጌዲዮን አመልክተዋል።
“ግብረሃይሉ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ክልል ውስጥ ፖሊስ ወይንም ሌላ ማንኛውም የጸጥታ ኃይል ትጥቁን እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል” ነው ያሉት፡፡ አካባቢውን ለመቆጣጠርና ሰላምን ለማስፈን አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ስልጣንም ተሰጥቶታልም ብለዋል።
ግብረሃይሉ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ማንኛውንም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባም ሆነ እንዳይወጣ ትዕዛዝ መስጠት እንደሚችልም ዶክተር ጌዲዮን አመላክተዋል።
ሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣልና የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን መከልክል እንዲችል ለግብረሃይሉ ስልጣን እንደተሰጠውም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።