አማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የመሥራች ጉባኤውን በውክልና ለማካሄድ መወሰኑን አደራጅ ኮሚቴው ገለፀ።

2247

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ባንኩ ምስርታ ጉባኤውን በውክልና ማካሔድ የወሰነበት ዋና ምክንያት የአባላቱ ቁጥር በጣም ከፍተኛ በመሆኑ እና ወቅቱም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ጉባዔ ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ብሏል።

የውክልና አሰጣጡ ከህዳር 1 እስከ ህዳር 30/2013 ዓ.ም ይጠናቀቃል፤ የምስረታ የጉባኤው ቀንም ወደፊት ይገለጻል ተብሏል።

የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ እንዳሉት በምስርታ ላይ ያለው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የአክሲዮን ሽያጭ ከጀመረበት ከነሃሴ 11/2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ድረስ የተፈረመው ወይም ቃል የተገባው የአክሲዮን ሽያጭ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ የተከፈለው ደግሞ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ መድርሱን አስታውቀዋል።

የባንኩ ምሥረታ በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መንገድ አክሲዮን መሸጥ በመቻሉ የባንኩን የካፒታል አቅም አሳድጓል ያሉት አቶ መላኩ በሽያጩ መሳተፍ ላልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

የአክሲዮን ሽያጭ የመዝጊያ የመጨረሻ ቀኑ ህዳር 21/2013 ዓ.ም መሆኑን ጠቁመው ባለው ቀናት አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ሰውም እንዲሳተፍ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በግዥውም የውጭ ዜጋ ሆነው የትውልደ ኢትዮጵያውያን መረጃ የያዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአቢሲኒያ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ እና ዳሽን ባንክ አክሲዮን መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ደግሞ በአባይ ባንክ ፣ በአቢሲንያ ባንክ፣ አክሲዮን ማህበር፣ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በዳሽን ባንክ ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል፣በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ በህብረት ባንክ፣ በንብ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም በቡና ኢንተርናሽናል መግዛት ይችላሉ ተብሏል።

የአክሲዮን ገዥዎች ቁጥርም ከ155 ሽህ በላይ መድረሱ ተመልክቷል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

Previous article“የአማራ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ የምንደራጅበት ጊዜ ነው” አቶ ሲሳይ ዳምጤ
Next articleበጎንደር ከተማ አስተዳደር ‹‹ደማችን ለመከላከያ ሠራዊታችን›› በሚል መልዕክት የደም ልገሳ ፕሮግራም ዛሬ ተጀምሯል፡፡