
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ሠላምና ደኅንነት ቢሮ የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በአማራ ክልል አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት መኖሩን አቶ ሲሳይ ዳምጤ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ መዋቅር የክልሉን ሠላምና ደኅንነት ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ ራሱን ከሕዝብ ጋር አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በትህነግ በሚመራው የጥፋት ቡድን በክልሉ በጎንደር ቀጣና በተለይም በጠገዴና ቅራቅር አካባቢዎች ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ማድረጉን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ ትንኮሳዎቹን የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ሚሊሻና ሕዝቡ በአስተማማኝ ሁኔታ ማክሸፉንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ የትህነግ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ አጀንዳ ቢሆንም የክልሉ የጸጥታ መዋቅር ሕዝቡን አሳልፎ ላለመስጠት ከምንጊዜውም በላይ በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተረጋጋ የሠላም ሁኔታ መኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡ ይህም የፖለቲካ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ የሐይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅንጅታዊ ሥራ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የአማራ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ የምንደራጅበት ጊዜ ነው” ብለዋል ቢሮ ኃላፊው፤ የሀሳብ ልዩነት ቢኖር እንኳን በአማራ ሕዝብ ላይ በሚደረግ ጥቃት ማንም ሊደራደር እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው ሊታገሉ እንደሚገባም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በሚጠይቃቸው ድጋፎች ሕዝብ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የክልሉ ሚሊሻና ልዩ ኃይልም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሲሳይ የትህነግ ቡድን አማራን ስትራቴጂያዊ ጠላት አድርጎ ተልዕኮውን ለማሳካት ቀን ከለሊት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቡድኑ በግንባር ብቻ ሳይሆን ብዙ አጀንዳዎችን በመስጠት ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ እየሠራም እንደሚገኝ ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት፡፡ ይህንን ሁኔታ መቀልበስ የሚቻለው በአንድነት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ ቢሮ ኃላፊው ከምን ጊዜውም በላይ የሕዝቡ አንድነትና ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡
ወቅቱ አርቆ ማሰብና ማስተዋልን የሚጠይቅ በመሆኑ የሕዝብ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ከስሜታዊነት ጸድቶ በዕቅድ ሊመራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሕዝብ ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት ለጸጥታ አካላት እንዲጠቁም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በተለይም የሐይማኖት ተቋማት ላይ ተመሳስለው በመግባት ጥቃት ለማድረስ የሚሞክሩ አካላት ስላሉ የየሀይማኖት አባቶች፣ አማኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የፖለቲካ መሪዎች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊው በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተጀመረው ሠላምና መረጋጋትን የማስፈን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ከአጎራባች ክልሎች ጋር መልካም ግንኙነትን በማጠናከር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአማራ ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ጥቃት እንዳያደርስም በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የሚቃጣ ጥቃትን ከመመከት ባለፈ ዳግም እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ርምጃ የመውሰድ አቅም እንዳለው በተግባር እየታዬ መሆኑንም ነው አቶ ሲሳይ የጠቀሱት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m