
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ በሚኖሩ ንፁኃን አማራዎች የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡ ለደረሰው ዘር ተኮር ጥቃት መንግሥት አሁንም አገር ውስጥ ትጥቅ አንግቦ የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን እና ህውሀትን ከመውቀስ አልወጣም፡፡ በዚህም አማራ ላይ ያነጣጠሩ ግድያወች መቀጠላቸውንና ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢወች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ለምን ተባብሶ ቀጠለ ሲሉ የሚጠይቁት አስተያየት ሰጭዎቹ መንግሥት የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን አለማስቆሙንም አንስተዋል፡፡
የታጠቁ የጥፋት ሀይሎችን ከመፈረጅ እና በመግለጫ ከማውገዝ ወጥቶ ድርጊታቸውን የሚመጥን እርምጃ መንግሥት እንዳልወሰደ የተናገሩት ነዋሪዎቹ አሁንም የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡
ማንነትን መሰረት በማድረግ በጅምላ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ድርጊትም ሁሉም የሰው ልጆች ሊያወግዙት እና ሊኮንኑት ይገባል፤ በተለይ ደግሞ ሀገር እንዲመራ እና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የህዝብን አደራ የተቀበለው መንግስት በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡
በኢትዮጵያ ምስረታ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የያዘው የአማራ ሕዝብ ዛሬም በየቦታው እየተጨፈጨፈ እና እየተፈናቀለ ነው፤ መንግሥት ሕግ የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ የአማራ ሕዝብ ራሱን አደራጅቶ ከጥቃት መከላከል እንዳለበትም አስተያየት ሰጭዎች ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፈንታሁን፡ ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ