“መንግስት እውነተኛ የህግ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን ይገባል” የሕግ ምሁራን

213

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ማንነት ላይ ያነጣጠሩ እና ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ነው፤ ጥቃቶቹ የተጠኑ እና ፈጻሚዎቹም የሚታወቁ መሆናቸው መንግስት በመግለጫው አረጋግጧል፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው የህግ ምሁራን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የጥቃቱ ጠንሳሾች ብሎ የጠቀሳቸውን ኦነግ ሸኔ፣ ትህነግ እና በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡

እንደ ሕግ ምሁራኑ ማብራሪያ በተለይ አማራን ዒላማ አድርገው የተፈጸሙ ጥቃቶች ወንጀለኞቹ ማንነታቸው እንደሚታወቅ እና የጸጥታ ሀይሉም ጥቃት እንደሚፈጸም አስቀድሞ መረጃ እንዳለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ሲያመለክት እንደነበር አንስተዋል፤ ይህም ሆኖ ጥቃቱንም መከላከል አልተቻለም፤ ጥቃት አድራሾቹም እውነተኛ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው አይደለም፤ እናም በየጊዜው ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ካሉ ጥቃቶች በስተጀርባ የሚያነሳቸውን ኦነግ ሸኔ እና ትህነግ በሽብርተኝነት ድርጅት ሊፈርጃቸው እንደሚገባ የሕግ ምሁራኑ አመላክተዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ ሰለሞን ጎራው እና የሕግ ጠበቃው በላይነው አሻግሬ እንዳሉት እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ማንነት ላይ ያተኮረ እና ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ንጹሃን ዜጎች ላይ ነው፤ ነዋሪዎቹ ምንም አይነት ትጥቅ ያልታጠቁ፣ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ እንደውም ጥቃቱን መከላከልም ሆነ መሸሽ አቅም የሌላቸው ህፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ናቸው፤ እንደዚህ አይነቱ ወንጀል ዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ህጎችን ጭምር የሚጥስ በመሆኑ በሽብር ወንጀል ስር የሚካተት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ድርጊቱ እንዲፈፀም ያደረጉት ትህነግ እና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኛ ድርጅት ሊፈረጁ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ሊዋጋቸው እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች በአወቃቀራቸው የተለያዩ ቢሆንም በዘር ማጥፋት ወንጀሉ ላይ በመተባበር የሚሳተፉ መሆናቸውን በመንግስት መግለጫዎች በተደጋጋሚ ሲነሳ እንደነበር የህግ ምሁራኑ ጠቅሰዋል፤ ነገር ግን ምንም እንኳን በፌዴሬሽን እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ተቀባይነት ባይኖረውም ትህነግ አሁንም በስልጣን ላይ ያለ፣ አድራሻው የሚታወቅ፣ የሕዝብ በጀት ጭምር ለእኩይ ተግባሩ የሚጠቀም መሆኑን አንስተዋል፤ የፌዴራል መንግስቱ በዚህ ቡድን ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱ በየጊዜው በንጹሃን ላይ ለሚፈጸመው ግፍ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ነው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ኦነግ ሸኔም ሆነ ትህነግ በቀጥታ ከመንግስት ጋር ባላቸው ቅራኔ ከመንግስት ጋር ችግራቸውን መፍታት ሲገባቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው አሸባሪነት እንደሆነ የሕግ ምሁሩ በላይነው አሻግሬ ነግረውናል፡፡

በዜጎች ላይ የተቃጣው ጥቃት የአማራ ብቻ ሳይሆን በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እንዲህ አይነቱን ጥቃት በማውገዝ ጥቃት አድራሾቹን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ሊደግፉ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

መንግስትም እነዚህን ድርጅቶች በአሸባሪነት በመፈረጅ በሚወስደው እርምጃም የጎረቤት ሀገራትን ብሎም ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማሳተፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፤ ችግሩን በትክክል በመረዳት በመንግስት መዋቅሩ ውስጥ ጭምር ያሉ አጥፊዎችን በመለየት እውነተኛ የሕግ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን እንደሚገባ ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- የማነብረሃን ጌታቸው

Previous articleመንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠየቀች፡፡
Next articleብሔርን ተኮር ያደረገ ጥቃት ሊቆም እንደሚገባ አስተየታቸውን የሰጡ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡