መንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠየቀች፡፡

279

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በወለጋ የተፈፀመውን ዘር ተኮር ጥቃት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥታለች፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እንዳሉት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም መንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ እና ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ ቤተ ክርስቲያኗ ትጠይቃለች፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ፣ በደቡብ ክልል ቤንችሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸው ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ታወግዛለች ብለዋል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ በዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ ድርጊቱን እንደሰማ የገለፁት ብፅዑነታቸው ጥቃቱ ሲኖዶሱና ቤተ ክርስቲያኗን በእጅጉ ያሳዘነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን በመግለጽ አውግዞታል ነው ያሉት።

ቤተክርስቲያኗም አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት በግፍ ለተገደሉና ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ልባዊ ሃዘኗን እንደምትገልፅ ተናግረዋል።

መላው ኢትዮጵያውያንም በወንድማማችነት፣በፍቅር፣ በአንድነት እና በመተሳሰብ እንዲኖሩ እና ለጋራ ሰላምና አንድነት እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

Previous article“ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል” የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ
Next article“መንግስት እውነተኛ የህግ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን ይገባል” የሕግ ምሁራን