
ፕሬዝዳንቷ ጥቅምት 22/2013 ዓ/ም በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ነዋሪ አማራዎች ላይ በተፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የፌስ ቡክ ገጽ ይፋ የሆነው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ሙሉ መልእክት፡-
የሰማሁት ዜና ልቤን ሰብሮታል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዛሬ ዓመት የተናገርኩትን ከመድገም ዉጪ ሌላ ቃላት የለኝም፡፡
ዘርና ሐይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውሉ ሲደረግ፣ ንጹሀን ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲንከራተቱ ስናይ ስሜትን ለመግለጽ ቃላት ያጥራል፤ ለቅሶ፣ ድንጋጤና ሥጋት የብዙዎችን በር አንኳኩቷል፤ ሃዘናቸው ሃዘኔ/ሃዘናችን ነው፤
ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፤ ሀገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፤ የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፤ ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል::