“በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ጭፍጨፋ ሁሉም አካል ሊያወግዘው ይገባል” አቶ አብርሃም አለኸኝ

672

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ እንደተናገሩት በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግልፅ ጥቃት የዓለም ህዝብ እና የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በይፋ ሊያወግዙት ይገባል፤ አማራ በሚኖርባቸው የሃገሪቱ ክፍሎች በፍቅር፣ በሰላምና በመረጋጋት እንዲኖር ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት፡፡

በወለጋ የተፈፀመው ግድያ በትህነግ እና ኦነግ ሸኔ እንደተፈፀመ ቢታወቅም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ከሃገር እና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም የሚሠሩ አካላት እንዳሉም ጠቅሰዋል፤ ይህንንም በጋራ መታገል እንደሚጠይቅ ነው ያስገነዘቡት፡፡

“እኛን መስለው ከኛ ጋር እየተወያዩ ከፓለቲካ መሪዎች ጋር እየዋሉ፤ ከመከላከያና ከጸጥታ አካላት ጋር እየመከሩ ነገር ግን መረጃ እየሰጡ ለህዝባችን እርስ በርስ መተላለቅ እና ሀገር እንዲጠፋና እንዳይቀጥል በማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ ከትህነግ እንዲሁም ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚሠሩ አካላት አሉ” ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት እና የመገናኛ ብዙኃን ጥቃቱን የተለያየ ትርጉም በመስጠት ለፖለቲካ ትርፍ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ለህዝብና ለሃገር በሚጠቅም መልኩ በግፍ ጥቃት ለደረሰበት እና በማንነቱ ብቻ ለሚገለለው የአማራ ማኅበረሰብ ድምፅ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Previous articleብሔር ተኮር ጥቃትን በዘላቂነት ለማጥፋት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ገለጸ፡፡
Next articleየአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በንፁሃን ላይ በተፈፀመው ግድያ የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ፡፡