ብሔር ተኮር ጥቃትን በዘላቂነት ለማጥፋት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ገለጸ፡፡

185

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) ጉባዔው በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዟል፤ የተሰማውን ሃዘንም ገልጿል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የጉባዔው መሪዎች መንግሥት የዜጎችን ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳልተወጣ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአማራ ክልል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ የቦርድ ሰብሳቢ መላከሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም ‘የተፈጸመው ብሔር ተኮር ግድያ አማራን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ነው’ ብለዋል፡፡

የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔው በድርጊቱ ማዘኑንም አስታውቀዋል፡፡ እንደ ሰብሳቢው ማብራሪያ እንደዚህ አይነት ድርጊት በኢትዮጵያውያን ባህል ያልተለመደ፤ ተደርጎም የማይታወቅ ነው፡፡ ጥቃቱ በአሳሳቢ ሁኔታ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች የታሪክ ተወቃሽ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ሐይማኖትና ብሔር ተኮር ግድያ መንግሥት አስቀድሞ እንዲከላከል የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔው በተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣቱንም አስታውሰዋል ፤ ይሁን እንጂ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ በየጊዜው መርዶ መስማት እየተለመደ መጥቷል ብለዋል፡፡ ‹‹ምን ብለን እንደምንናገር፣ ለማን እንደምንጮህ፤ አቤቱታችንን ለማን እንደምናቀርብ ግራ ገብቶናል›› በማለትም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ችግሩን አድበስብሶ ከማለፍና ምክንያት ከመደርደር ወጥቶ ቀድሞ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የጉባዔው ምክትል ሰብሳቢ ሸህ ሰዒድ መሐመድ “በንጹሃን አማራዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እናወግዛለን” ብለዋል፡፡ መንግሥት አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ሙሉ አቅም ቢኖረውም ወደተግባር ለመቀየር ውስንነት መስተዋሉንም አመላክተዋል፡፡ “እንደሐይማኖት ተቋማት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ማውገዝ እያሳፈረን ነው” ያሉት ሸህ ሰዒድ ችግሩ መንግሥት ሚናውን በአግባቡ ባለመወጣቱ የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ችግሮች ተመሳሳይ ምክንያት መሰጠቱ አሳማኝ እንዳልሆነ በማንሳትም ርምጃ አለመወሰዱን በክፍተት አንስተዋል፡፡ በቀጣይ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ሸህ ሰዒድ ተናግረዋል፡፡ በመንግሥትና በጸጥታ መዋቅር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡትንም መጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትና የሐይማኖት ጉባዔው የቦርድ ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ በበኩላቸው ንጹሀንን በጅምላ መጨፍጨፍ አሳፋሪ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ ችግሩ እየተደጋገመ በመሆኑም ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ከጀርባ የሚሠሩ ኃይሎችን አደብ ማስገዛትና የጸጥታ ስጋቱን ማስወገድ እንደሚጠበቅበት አንስተዋል፡፡

የጸጥታ አካላትን ማሰማራት እንደተጠበቀ ሆኖ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ሕዝብ እራሱን እንዲጠብቅ ማስተማርና ማደራጀት እንደሚገባም መጋቢ ገብሬ ተናግረዋል፡፡

በየጊዜው የሚስተዋለውን ብሔር ተኮር ጥቃትን በዘላቂነት ለማጥፋት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የሐይማኖት ጉባዔው አስታውቋል፡፡ መንግሥታዊ አወቃቀሩ ሰው በጎራ እንዲፈራረጅ ማድረጉን የገለጹት የጉባዔው መሪዎች ሀገራዊ አስተሳሰብን ለማጎልበት አዲስ የፖለቲካ አካሄድ ሊዘጋጅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article‹‹ህፃናት እየተራቡ ነው፤ መንግሥት ሊደርስልን ይገባል›› በጉሊሶ ወረዳ ጥቃት የደረስባቸው ነዋሪዎች ኦነግ ሸኔ ዛሬ ጠዋት በንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡
Next article“በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ጭፍጨፋ ሁሉም አካል ሊያወግዘው ይገባል” አቶ አብርሃም አለኸኝ