
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ምሁራን መማክርት በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በአማራዎች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የምሁራን መማክርቱ በመግለጫው እንዳለው ጥቃቱን ማንም ይፈፅመው ማን መንግስት የማስቆም ግዴታ አለበት።
በአማራ ላይ የተቃጠውን ጥቃት መንግስት ማስቆም ካልቻለ ኢትዮጵያን ወደ ማትመለስበት ችግር ይከታታል፤ መንግስት የህዝቦችን ደህንነትን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ቢያውቅም ችላ በማለቱ በተለይም በአማራ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ቀጥለዋል፤ ይሄም የአማራን ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ አስቆጥቷል፤መንግስት ጉዳዩን በውል ሊረዳው ይገባል ብሏል።
መንግስት የአማራን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ተጨባጭ ሥራ ሰርቶ ማሳየት ይገባዋልም ነው ያለው በመግለጫው።
አማራ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት የአንበሳው ድርሻ እንደተጫዎተ ቢታወቅም አሁን ላይ አንገቱን ቀና እንዳይደረግ ከሁለተኛም ዜጋ ባነሰ ሁኔታ እንዲሆን እያደረገ ነው፤ይሄ ኢትዮጵያን ያፈርሳል፤መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሩን ከማውገዝ ባለፈ ሊከላከል ይገባልም ብሏል፡፡
ችግሩ ሰፍቶ ሁላችንም ወደማያባራ እልቂት ከመዳረጉ በፊት ሊታሰብበት እነደሚገባ አመላክቷል፡፡
የፌድራል መንግስት ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ በማመን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የምሁራን መማክርቱ ገልጿል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ – ከአዲስአበባ