መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እያራመደ ያለው ተገቢ ያልሆነ የዲሞክራሲ ልምምድ እና ሆደ ሰፊነት የአማራ ሕዝቦችን ለዘር ተኮር ጥቃት እያጋለጠ ነው ተባለ፡፡

215

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ መንግሥት እያሳየው ያለው ለዘብተኛ አቋም፣ መስመሩን እየሳተ የዴሞክራሲ ልምምድ እና ሆደ ሰፊነት አማራ ተለይቶ እንዲጠቃ ምክንያቶች መሆናቸውን አብመድ ያነጋገራቸው ምሁራን ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን የሚስተዋለው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ምንጩ ወጥ ያልሆነ እና አውዳዊ ፍች ከጎደለው የብሔር ብያኔ የሚነሳ መሆኑን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አንተነህ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ትርጓሜው ‹‹ዘር›› የሚል ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጥቁር ዘሮች ናቸው፤ በዓለም ላይ የዘር ልዩነት ውስን ሲሆን በብሔር ደረጃ ግን እልፎች ተስተውለዋል፤ በበርካታ ሃገራት ብሔርን መሰረት አድርገው የተነሱ የዘር ግጭቶች መነሻ ያደረጉት ‹‹ነጭ እና ጥቁር›› በሚል መለያ ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን በፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመመደብ አገልግሎት ላይ የዋለው የብሔር ብያኔ ግን ወጥ እና ተገቢ ፍቺ የተሰጠው አለመሆኑን ነው አቶ አንተነህ የተናገሩት፡፡

ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ለክልሎች የተሰጠው ስልጣን ዜጎች ሀገርን ቆራርሶ የመመልከት ሥነ ልቦናዊ ስሪት እንዲያዳብሩ እንዳደረጋቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ገልጸዋል፤ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ሕዝቦችንም ለተደጋጋሚ ጥቃት ተጋላጭ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

ምሁሩ እንዳሉት በአማራ ክልል የሚኖር ከየትኛውም አካባቢ የሚመጣ ኢትዮጵያዊ በክልሉ እስከኖረ የክልሉ ባለቤት ነው፤ በአንፃሩ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ሕጋዊ ውክልና እንዳይኖራቸው ከሕገ መንግሥቱ በተፃራሪ ክልሎች ያወጡት ሕገ መንግሥት ስለሚከለክል ሕጋዊ ውክልና እንዳይኖራቸው አድርጓል፤ ይህም ለተደጋጋሚ ለማንነት ጥቃት ሰለባ አጋልጧቸዋል፡፡

ሌላው የሕግ ባለሙያ አዲሱ ገነት መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር እንዲኖር ካስፈለገባቸው ጉዳዮች መካከል ዜጎችን ማክበር እና ጥበቃ ማድረግ ቀዳሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ቢኖርበትም እሱን ግን እየተገበረ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ ‹‹የዲሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ የዜጎችን የመኖር መብት እየጣሱ የሚመጣ አይደለም›› ብለዋል አቶ አዲሱ።

በልምምድ ውስጥ የሚፈጠሩት ስህተቶች ሲበራከቱ እና ተበዳይ የሆነ ማኅበረሰብ ሲፈጠር ወደኋላ ለመመለስ እንደሚያስገድድ ነው ያስረዱት፡፡ የፖለቲካ ትዕግስት በግለሰቦች እንጂ በርዕዮተ ዓለም ወይም መንግሥትን በሚመራ ፓርቲ ውስጥ ሊኖር እንደማይገባም አስገንዝበዋል። ‹‹መንግስት እያሳየው ያለው ለዘብተኛ አቋም፣ መስመሩን የሳተ የዴሞክራሲ ልምምድ እና ሆደ ሰፊነት አማራ ተለይቶ እንዲጠቃ ምክንያቶች ሆነዋል›› ነው ያሉት የሕግ ምሁሩ፡፡

እየተፈጠረ ለሚገኘው ከሰብዓዊነት የወጣ ዘርን መሰረት ያደረገን ጥቃት ለማስቆምም መንግስት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር፣ አጥፊዎችን ለይቶ ለሕግ እንዲያቀርብ፣ የመዋቅር ለውጥ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግስትም በሃገር ደረጃ ጠንካራ የፖለቲካ ካፒታል በመገንባት ሕዝቡም ተደራጅቶ እራሱን ከጥቃት መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለተደጋጋሚ ግጭት ምክንያት የሆኑ ሕጎችን እና መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን መፈተሽ እና መስተካከል እንዳለባቸውም ምሁራኑ አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“እየደረሰ ያለው ጥቃት ‘የንፁሀን ህልፈት’ እየተባለ የሚሽሞነሞን ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሕግ ይቅርታ እና ምህረት እንኳን የማያሰጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡” የርዕሰ መስተዳድሩ የህግ አማካሪ መርኃጽቅ መኮንን
Next articleበምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በአማራዎች ላይ በተፈፀመው ጥቃት መንግስት ተጠያቂ ነው ሲል የአማራ ምሁራን መማክርት ገለጸ።