“ዘር ተኮር ጥቃቱ ያስተማረን እውነት ቢኖር የለውጥ ሃይሉን ሃሳብ ከልብ የሚደግፉት ውስኖች ብቻ እንደሆኑ ነው” ምሁራን

231

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በአፋቸው የሚያነበንቡት የትየለሌ ቢሆኑም በልብ ማኅተማቸው ያተሟት ግን አልፈዋል ወይም ውስኖች ናቸው፡፡ ጊዜያዊ ጥቅም እና የጋራ ጠላት የሚያስተሳስራቸው ቡድኖች በየጊዜው ጋብቻ ቢፈፅሙም ለፍች ግን ጀንበር እስክትጠልቅ እንኳን አይጠብቁም፡፡ ጥምረት እና ውህደት አለ እንኳን ከተባለ በመሪዎች እንጅ በተከታዮቻቸው ዘንድ አልታየም፤ መሪዎቹም እንመራዋለን ከሚሉት ጎጥ ሲደርሱ በጋራ የመከሩትን አፍርሰው ወደ እውነተኛው ስሪታቸው ሲመለሱ ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡

ዘር ተኮር ጥቃት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ሀገር ቤት ቢደርስም ወደተግባር የተለወጠው ግን ትህነግ መሩ ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ሲገባ ነበር፡፡ በአንድ እጃቸው መሳሪያ በሌላ እጃቸው የብሔር ጥያቄን ያነገቡት ገንጣይ አስገንጣዮቹ ስልጣን በያዙ ማግስት ኢትዮጵያዊ ስሪት እና ስነ ልቦና አለው ባሉት የአማራ ህዝብ ላይ ግፍ ሲፈፅሙ
ህገ መንግስታቸውን እንኳን እስኪያፀድቁ መጠበቅ አላስቻላቸውም፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህሩ አንተነህ ተስፋሁን እንደሚሉት “በአማራ ህዝብ ላይ በየቦታው የሚፈፀሙት ጥቃቶች ሦስት ባለቤት አላቸው፤ በየቦታው የተለያየ ስያሜ የሚሰጣቸው ጥቃት ፈፃሚዎች፣ ከጥቃቱ ፈፃሚዎች ጀርባ ያሉ ስትራቴጅስቶች እና ይህን መሰል አስተሳሰብ ያለው ስርዓትን የፈጠሩ ሃይሎች” ሲሉ በሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡

“በአማራ ላይ እየተፈፀሙ ካሉ ዘር ተኮር ጥቃቶች በፊት ፍረጃን የቀደሙ ትርክቶች፣ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች ስር እንዲሰዱ መደረጋቸውን መምህር አንተነህ ገልጸዋል፤ አሁን የምናየው የትናንቱን ሥራ ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

“በየትኛውም ዓለም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በአንድ ሌሊት አልተፈፀሙም፤ አይፈፀሙምም” የሚሉት የህግ ባለሙያው አዲሱ ገነት “የዘር ማጥፋት ወንጀል የተከታታይ ጥቃቶች የልምምድ ውጤት ነው” ባይ ናቸው፡፡ “በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ የዘር ማጥፋት ሂደት መሆኑን መንግስት በቅድሚያ እውቅና ሊሰጥ ይገባል፤ ከእውቅና በኋላ እርምትም ሆነ እርምጃ መውሰድ ቀላል ይሆናል ” ነው ያሉት፡፡

ምሁራኑ እንደሚሉት እየተፈጠረ ያለው ዘር ተኮር ጥቃት የሚያመላክተው እውነት ቢኖር በለውጥ ሃይሉ ውስጥ የሰላም፣ የእኩልነት፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያዊ አንድነት እውነተኛ ፍላጎት ያላቸው ውስን ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ነው፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በየጊዜው ከሚፈጠረው ችግር በስተጀርባ እጃቸው እንዳለበት እና የየራሳቸው ድብቅ ዓላማ እንዳላቸው አመላካች ጉዳዮች መኖራቸውን ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አብነት አድርገው ጠቅሰዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“አማራዊ ማንነታችን የጥቃት ምንጭ መሆኑ ሊቆም ይገባል” ሲሉ የንግድ ሚኒስትሩ አሳሰቡ፡፡
Next articleበምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንፁሀን ዜጐች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል፡፡