
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በተያዘው ዓመት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ መዝገቡ አንዷለም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም 98 በመቶ የሚሆነው ለመማሪያ ክፍል ግንባታ እንደሚውል አመላክተዋል፡፡ ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ይሕንን ያሉት ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር ሲወያዩ ነው፡፡
በውይይቱ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በክልሉ ምንም ያህል የተፈጥሮ ፀጋ ቢኖርም በትምሕርት የታነፀ ትውልድ ወደ ጥቅም ካልቀየረው ምንም ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የትምሕርት ተደራሽነት እና የትምሕርት ቤቶች የጥራት ደረጃ በዓለምአቀፍ መስፈርታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ባለሃብቶች ለዘርፉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ውይይቱ ትኩረቱን ያደረገው ባለሀብቶች ግምባር ቀደም ተዋናይ የሚያደርጋቸውን ጠንካራ የአልማ ኮርፖሬት አደረጃጀት መፍጠር ላይ ነው፡፡ አደረጃጀቱም ማኅበሩን በዘላቂነት እንዲደግፉ የሚያስችል ነው፤ አቶ መዝገቡ የክልሉን ሁለንተናዊ ችግር ለመፍታት ትውልዱን ማስተማር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፤ ለዚህም የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ በፍጥነት ማስተካከል የማሕበሩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ነው ያስታወቁት ፤ እስከ 2014 ዓ.ም ደረጃቸውን ያሟሉ ትምሕርት ቤቶችን ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፤ ለዚህም የባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የክልሉ መንግሥት ለትምሕርት፣ ለጤናና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከመደበው የካፒታል በጀት ውስጥ 54 በመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው በአልማ ነው፡፡ በተለይም ለትምሕርት ዘርፉ 65 በመቶ ድርሻ እንደሚወስድ ተጠቅሷል፡፡
ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲኖረው የኮርፖሬት አባላት አደረጃጀት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የአልማ የኮርፖሬት አደረጃጀት ጥሩ ውጤት ማስገኘቱ ተመልክቷል፡፡
አደረጃጀቱን በባሕር ዳር ለመጀመርም ነው ስምምነት ላይ የተደረሰው፡፡
በውይይቱ የአልማ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የትምሕርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) በክልሉ የትምሕርት ሽፋንና የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከትምሕርት ቤት የደረጃ መስፈርቶች መካከል የትምሕርት መሠረተ ልማት 25 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝም ተናግረዋል፡፡
በተያዘው ዓመት የሚከፈቱትን 25 አዳዲስ ትምሕርት ቤቶች ጨምሮ 618 የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች አሉ፤ ይሕም 30 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ለሚኖርበት ክልል በጣም አናሳ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ብቃት ያላቸው የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች በኑሮ ውድነት ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ለመማር ሲቸገሩ መስተዋሉንም ነው ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት፡፡
ክልሉ ለሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ግንባታ የመደበው 88 ሚሊዮን ብር ነው፤ ይሕም ከ7 ትምሕርት ቤቶች በላይ መሥራት እንደማያስችል አብራርተዋል፡፡
በአልማ በኩል ከ70 በላይ ትምሕርት ቤት መገንባት እንደሚቻል ጠቅሰው ለዚህም የሕዝብ ድጋፍ እና የባለሀብቶች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም ለትምሕርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አድንቀዋል፡፡ የአባላት ቁጥር መጨመር ማሕበሩ ቀጣይ የሚያከናውናቸውን የልማት ሥራዎች እንዲያሳድግ ይረዳል ብለዋል፡፡ አሠራሮች ግልጸኝነት ያላቸው እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮርፖሬት አባላት አደረጃጀት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአልማ የኮርፖሬት አደረጃጀት በደሴ እና በኮምቦልቻ ካሁን ቀደም ተጀምሯል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4