የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የበርሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

239

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የበርሃ አንበጣ መንጋ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ የጉዳት መጠኑ እየታየ ቀጣይነት እንደሚኖረው ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በምስራቅ አማራ በርካታ አካባቢዎች በመስከረም መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ የበርሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱን መዘገባችን ይታወቃል፡፡ የበርሃ አንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በሕዝቡ፣ በአጋር አካላትና መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግም በበርካታ አካባቢዎች በሚገኝ ሰብል ጉዳት አድርሷል፡፡

የአንበጣ መንጋው አሁንም ሙሉ በሙሉ ያልተወገደ ሲሆን በሳይንሳይዊና ባህላዊ መንገድ የሚካሄደው የመከላከል ሥራ እንደቀጠለ ነው፡፡

አልማ በበርሃ አንበጣ ሰብላቸው ለተጎዳባቸውና አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች 800 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የአልማ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አለማየሁ ሞገስ ለአብመድ እንደገለፁት “አሁን የተደረገው ድጋፍ በበርሃ አንበጣ መንጋው በሰብላቸው ላይ ጉዳት ላደረሰባቸውና አፋጣኝ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚውል ነው።” በቀጣይም የበርሃ አንበጣው ያደረሰው ጉዳት እየታየ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ሲጀመር የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ይገጥማቸው ይሆናል ተብሎ ለሚታሰቡ ተማሪዎች አልማ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

አካባቢው ከተፅዕኖ ወደ ሌላ ተፅዕኖ የተሸጋገረ በመሆኑ በተማሪዎች ሥነ ልቦና ላይ ጫና እንዳይፈጥር ሲባል 260 ሺህ ደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ መደረጉን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

“አልማ የሦስት ዓመታት የለውጥና ስትራቴጂ ዕቅድ ነድፎ በትልልቅ ጉዳዮች ላይ ወደሥራ ቢገባም፤ ለክልሉ ማኅበራዊ ልማት እስከተቋቋመ ድረስ በሕዝቡ ላይ የሚደርሱ ማኅበራዊና ተፈጥሯዊ ጫናዎችን እንዲሻገር ለመደገፍ ይሠራል ነው” ያሉት አቶ አለማየሁ፡፡

ድጋፉ በበርሃ አንበጣ መንጋው ጉዳት ለደረሰባቸው የምስራቅ አማራ ሁሉም አካባቢዎች ተሰራጭቷል፡፡ በተመሳሳይ ዜና ዳሽን ቢራ ፋብሪካ በወልድያ ከተማ ለሚገኙ 200 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ፋብሪካው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች አንድ አንድ ደርዘን ደብተር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን መሰል ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም ዞኖች እያሰራጨ መሆኑንም የፋብሪካው የወልድያ ከተማ የገበያና ማስታወቂያ ባለሙያ ሰሎሞን አረጋዊ አስታውቀዋል፡፡

ዳሽኝ ቢራ ፋብሪካ ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ነግረውናል፡፡ ዳሽን ቢራ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በቀጣይም ሕዝብን በሚጠቅሙ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከወልዲያ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4

Previous articleየኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በአንድ ክፍል እስከ 30 ተማሪዎችን ለማስተማር በሚደረገው ጥረት የመማሪያ ክፍል ጥበት፣ የመቀመጫ ወንበር እና የመምህራን እጥረት ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleየጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከምርጥ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተካተተ፡፡