የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በአንድ ክፍል እስከ 30 ተማሪዎችን ለማስተማር በሚደረገው ጥረት የመማሪያ ክፍል ጥበት፣ የመቀመጫ ወንበር እና የመምህራን እጥረት ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

207

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት በሽታውን በመከላከል ለማስጀመር የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በትምህርት ዙሪያ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የክልሉን ትምህርት በመደገፍ በኩል እያደረጉት ያለውን ሥራ አድንቀዋል፡፡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለትምህር ቤቶች ላቀረቡ ድርጅቶችም ምሥጋና አቅርበዋል።

በመንግሥት፣ በኅብረተሰብ ተሳትፎና በሌሎች አካላት ተጨማሪ 5 ሺህ 464 አዳዲስ መማሪያ ክፍሎችን መገንባት ቢቻልም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በአንድ ክፍል እስከ 30 ተማሪዎችን ለማስተማር በሚደረገው ጥረት የመማሪያ ክፍል ጥበት፣ የመቀመጫ ወንበር እና የመምህራን እጥረት ችግሮች መሆናቸውን የቢሮ ኃላፊው ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።

የ2013ዓ.ም የትምህርት ሥራን ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ችግሮችን ተገንዝበው በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ዶክተር ይልቃል ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉት የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደር የአማራ ክልል የፕሮግራም ዳይሬክተር ካሳ አስማረ ድርጅታቸው በሚሠራባቸው ከተሞች በ25 ሚሊዮን ብር ለትምህርት ቤቶች የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብዓቶችን፣ ወንበሮችን እና አቅም ሌላቸው ወላጆች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ቢሮን ወክለው የተገኙት አቶ ጌታለ መንጋው ደግሞ በክልሉ 25 ወረዳዎች ድርጅታቸው ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን፣ ቤተ መጻሕፍት፣ መፀዳጃ ቤቶችን፣ የሙቀት መለኪያዎችን እና የንጽሕና መጠበቂያዎችን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን የአማራ ክልል 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። እነዚህን ተማሪዎች አንድ ክፍል ለ30 ተማሪ በሆነ ምጣኔ ለማስተማር ከ203 ሺህ 330 በላይ የመማሪያ ክፍሎች ያስፈልጋሉ፡፡ በሁለት ፈረቃ ከሆነ ደግሞ የሚያስፈልገው የመማሪያ ክፍል ብዛት 101 ሺህ 660 አካባቢ ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡- ደመቀ ቦጋለ

Previous article756 የምግብ አይነቶችን መዝግቦ ለኅብረተሰቡ መረጃ ማቅረቡን የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
Next articleየአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የበርሃ አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡