
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን በ2013 በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት በምግብ ጥራትና ደኅንነት፣ በመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች ጥራት ደኅንነትና ፈዋሽነት ላይ የተሰሩ የቁጥጥር ሥራዎችና የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብና የመድሀኒት አቅርቦቶችን ደኅንነትና ጥራት ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ 756 የምግብ አይነቶችን መዝግቦ ለኅብረተሰቡ በመረጃ መረብ ማሳወቁን ገልጿል፡፡ የምግብ ጥሬ ዕቃዎችን ጨምሮ 573 ሽህ ቶን ምግብ ባለፉት ሦስት ወራት ጥራታቸውን በማረጋገጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉንና ሌሎች ከ24 ነጥብ 2 ቶን በላይ የምግብ ሸቀጦች ማገዱንም ባለስልጣኑ አሳውቋል።
በገበያ ላይ ከዋሉ በኋላ በተደረገ የገበያ ጥናት በአስመጭዎች፣ በአምራቾች እና በአከፋፋዮች ላይ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦችና መድሀኒቶች ያከፋፈሉ፣ በቂ የምግብና የመድሀኒት ማቆያ የሌላቸው፣ የጥሬ ዕቃ አያያዝ ችግር ያለባቸውን እርምጃ እንደወሰደባው ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡ የንግድ ፍቃዳቸውን የማገድ፣ የመሰረዝ እና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን በመግለጫው ተነስቷል፡፡
ባለስልጣኑ በ14 ከተሞች አደረኩት ባለው ድንገተኛ ፍተሻ 91 የሚደርሱ የምግብ ምርቶችን ማገዱን እና ለኅብረተሰቡም በተለያየ መንገድ ማሳወቁን ገልጿል። በተለይ በመድሀኒቶች ላይ የሚታየውን የጥራትና የደኅንነት ጉዳይ ለማረጋገጥ በ (i veryfiy apps) የሞባይል መተግበሪያ ወይም በ8482 የነጻ የስልክ መስመር በመጠቀም የማረጋገጥ ሥራ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
የዘርፉ ፈቃድ ሳይኖራቸው ምርትን ማከማቸት፣ ጥራታቸውን ያልጠቁ ምርቶችን ይዞ መገኘት፣ የሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋት፣ የቅንጅት ሥራዎች አለመጠናከር፣ አምራቾችና አከፋፋዮች የተስማሚነት ምዘና ሳያልፉ ሕገ ወጥ ሥራ ላይ መሰማራት ፈተና እንደሆነበት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል። ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ሲሆን ይህን ለመደገፍም የአሰራር መመሪያ መዘጋጀቱም በመግለጫው ተነስቷል።
አጥፊዎችን በሕግ ለመጠየቅ ሥራዎች በባለስልጣኑ የሕግ ክፍል በኩል እየተሰሩም እንደሆነ ተገልጿል። ባለስልጣኑ አሰራርን የማዘመንና ክፍተቶችን ፈትሾ ለሕዝብ የተሻለ አገልግሎት ለመዘርጋት እየሰራ ነው ተብሏል፤ የኅብረተሰቡ እገዛ እንደሚያስፈልገውም ጥሪ አቅርቧል፡፡ በተለይ ከኮሮናቫይረስ መከላከል ጋር በተያያዘ ቁሳቁስ ጥራት ማረጋገጥ፣ የመድሀኒት የግዥ ሥራዎችን ማዘመን እና የመድሀኒት አቅርቦቱ የተሟላ እንዲሆን ሰፊ ሥራ መሰራቱ ተገልጿል፡፡ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብ ተቋማት ዳይሬክተር በትረ ጌታሁን ከእንጀራ፣ ማርና ቅቤ ጋር ባእድ ነገር በመጨመር የሕዝብ ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ችግሮችን ሲመለከት ጥቆማውን 8482 ነጻ የስልክ መስመር በመጠቀም እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ገበያ ላይ በሚገኙ 14 የለውዝ ምርቶች ላይ በተደረገው ምርመራ ከፍተኛ የሆነ (አፍላ ቶክሲን) ስለተገኘባቸው እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ችግር ያለባቸውን ምርቶች ስያሜ ከባለስልጣኑ ድረ-ገጽ መረጃ ማግኘት እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብ ደኅንነት ፖሊሲ በማዘጋጀት ችግሮችን በአሰራር ለመመለስ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡-ጋሻው ፈንታሁን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4