
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2013 (አብመድ) የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበጀት ዓመቱ ከዘርፉ የውጭ ንግድ ገቢ 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ባለፈው የክረምት ወራት የቆዳና ሌጦ ዋጋ በመውረዱ በተለይ ጥሬ ሌጦ በየሜዳው ወድቆ እንደሚስተዋልና ምክንያቶቹን አቅርበን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችና የሚመለከታቸው አካላት ምን እየሰሩ እንደሆነ መረጃ አሰባስበናል፡፡
የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዝዳን ብርሃኑ አባተ እንደ ሀገር ወደ 7 ሺህ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢ ነጋዴዎች እንዳሉ ነግረውናል፡፡ ምርቱን የሚቀበሏቸው ፋብሪካዎች የመቀበል ፍላጎት መቀነስ በገበያ ላይ ዋጋው እንዲቀንስ እንዳደረገው ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ምንም እንኳን አሁን ችግሩ የተቀረፈ ቢሆንም ቆዳ የተወሰነ ቀን ሳይበላሽ ለማቆየት የሚጠቀሙበት ጨው አቅርቦት ችግር እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካዎች ማኅበራት ዋና ጸሐፊ ዳንኤል ጌታቸው እንዳሉት እንደ ሀገር 30 የሚሆኑ የቆዳ ፋብሪካዎች ቢኖሩም የገንዘብ፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የገበያ፣ የጥራት እና የግብአት ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ እናም በሙሉ አቅማቸው አለመስራታቸው ለቆዳና ሌጦ ምርቱ ብክነት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳንኤል እንደተናገሩት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአሜሪካ፣የፈረንሳይ፣ የኤሲያ እና የአፍሪካ ሀገራት ገበያ እዲዳከም አድርጎታል፡፡ ዘርፉ ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከንግድ፣ ከወጪ እና ገቢ ንግድ፣ ከፋይናንስ እና መሰል ፖሊሲዎች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑ የሁሉንም ቅንጅት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ችግሩን ለመፍታት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት አበረታች መሆኑንና በቅርቡ ዘርፉን የሚታደግ መፍትሄ ለማግኘት ተቀናጅተው እየሠሩ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ብርሃኑ ሰርጃቮ በእንስሳት ሀብት ረገድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ስድስተኛ መሆኗን በመጥቀስ በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት አስረድተዋል፡፡
“ነገር ግን ባላት ሀብት ልክ አልተጠቀመችም፤ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፤ የመጀመሪያው የጥራት ችግር ነው፤ በሀገራችን ያለው ዘልማዳዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴ ለቆዳና ሌጦ ምርቱ ጥራት ችግር እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፤ እንስሳቱ በተለያዩ በሽታዎች ይጠቃሉ፤ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ዘፈቀዳዊ ነው” ሲሉ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ለቆዳና ሌጦው ጥራት የእንስሳቱ እንክብካቤ፣ የጤና ሁኔታ፣ የእርድ እና ቆዳና ሌጦው የሚፈለግበት ቦታ እስኪደርስ ያለው ሂደት የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ማግኘት አላስቻሉም ባይ ናቸው አቶ ብርሃኑ፡፡ ይህንን የጥራት ጉደለት ለማስተካከል የተለያዩ የፖሊሲ እርምት እርምጃዎች በመንግስት እየተወሰዱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ለባለሞያዎች ስልጠና ይሰጣል፣ ለፋብሪካዎች የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል፣ በዘርፉ ጥናት በማካሄድ የምክር አገልግሎት ይሠጣል ብለዋል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተማሪዎችን ማስመረቅ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡ ከ43 በላይ በቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች በቆዳና ሌጦ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስልጠና እየሰጡና በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል እያፈሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
“የእንስሳት የአረባብ ዘዴ እንዲሻሻል ከግብርና ሚኒስቴርና መሰል ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትኩረት እየሰራን ነው” ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡ እንደ ኢንሰቲቲዩቱ መረጃ በሀገሪቱ ቆዳና ሌጦ የማልፋትና የማለስለስ ሥራ የሚሠሩ ወደ 30 የሚሆኑ ፋብሪካዎች አሉ፤ ስድስቱ በአማራ ክልል ይገኛሉ፤ እነዚህ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ቢችሉ በዓመት ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት መቀበልና ማምረት ይችላሉ፤ ነገር ግን ከመላው ሀገሪቱ ተሰብስቦ ወደ ፋብሪካዎቹ እየቀረበ ያለው የቆዳና ሌጦ ምርት በዓመት ከ21 እስከ 24 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡
የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዘርፉን ለመታደግ ሌላኛው መፍትሄ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ነው፡፡ ፋብሪካዎቹ አሁን ማምረት ከሚችሉበት አቅም ከ25 ወደ 80 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የሚቀርብ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት በቂ ባለመሆኑ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር ለመቀበል የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም አለማምረታቸው፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሀገራት የንግድ ልውውጥ መቀነስ፣ የአሜሪካ እና ቻይና የንግድ ውዝግብ በዘርፉ ያሳደረው አሉታዊ ተጽኖ ቀላል የሚባል አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርቱን አልፍተውና አለስልሰው ወደ ተቀባይ ሀገራት መላክ አለመቻላቻው ተጨማሪ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት ከገበያው መቀበል አልቻሉም፤ ቆዳና ሌጦ በባህሪው ለረጅም ጊዜ መከማቸት አለመቻሉ ነጋዴዎች እንዳይገዙና ሻጩም ተቀባይ አጥቶ በየሜዳው እንዲባክን ሆኗል ብለዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢ ነጋዴዎች ፋብሪካ ተከራይተው የተወሰነ ደረጃ ማልፋትና ማለስለስ ሂደትን በመከወን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ማድረግ፤ ይህን ካልቻሉ ኤግል ለተባለ መንግስታዊ ድርጅት እንዲያቀርቡና ቆዳው የተወሰነ የምርት ሂደትን አልፎ ገበያ አስኪአገኝ ድረስ መቆየት የሚችልበትን መንገድ መፈለግ፤ በሀገሪቱ ያሉ ፋብሪካዎች ይህንን ሂደት እንዲከውኑ ነገር ግን የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ከባንኮች ጋር ብድር እንዲመቻችላቸው ማድረግ እና መሰል የመፍትሔ ሀሳቦችን ኢንስቲትዩቱ ከኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተጠንተው ለመንግስት ቀርበው ወደ ትግበራ መግባታቸውን አቶ ብርሃኑ ነግረውናል፡፡
በሀገር ውስጥ ያሉ የለፋ እና የለሰለሰ ቆዳ በግብአትነት የሚጠቀሙ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕረያዞችን በመደገፍና ዘርፉን እንዲነቃቃ ማድረግ ሌላኛው አማራጭ መፍትሄ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከቆዳ ፋብሪካዎች የለሰለሰ እና የለፋ ቆዳ እንዲያገኙም ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ የአቅም ግንባታ ስልጠና ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የመስሪያ መሳሪያዎችን ማሟላት፣ ቦታ ማመቻቸት ወዘተ ለኢንተርፕራይዞቹ ከሚደረጉላቸው ድጋፎች መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት ወደ ውጭ በተላከ የቆዳና ሌጦ ምርት 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ምርት ለማግኘት ታቅዶ 74 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው የተገኘው፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ የቆዳና ሌጦ ምርት፣ ያለቀላቸው እንደ ጫማ፣ ጓንት፣ ቦርሳ፣ አልባሳት እና መሰል ምርቶች 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት እቅድ መያዙን ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m