
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) ዳክሮክ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የንግድ ፍቃድ ሳያወጣ የተለያየ የንግድ ምልክት ያላቸው የምግብ ዘይቶችን በመቀላቀል (በማዋሃድ)ና ኤርካና ዴዚ የተባሉ የንግድ ስያሜዎችን በመስጠት ለገበያ ማቅረቡን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል። በዚህም በወንጀል ተግባር ላይ መገኘቱ ተነግሯል።
ማኅበሩ በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ በኢንዱስትሪ መንደር አካባቢ በተከራየው መጋዘን ውስጥ ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን መመልከት ችለናል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኢንስፔክሽን ባለሙያ አበበ አዲሱ ዳክሮክ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በምግብ ምርቶች አስመጪነት የንግድ ፍቃድ ቢኖረውም በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ግን የንግድ ፍቃድ እንዳላወጣ አስታውቀዋል።
በምግብ ምርቶች አስመጪነት ፍቃድ ቢኖረውም የተለያዩ የምግብ ዘይቶችን በመቀላቀልና ያለፍቃድ የራስ ንግድ ምልክት በመፍጠር ለገበያ ማዋል ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን አቶ አበበ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የሰሜን ምእራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሙሉጌታ ቆየ ከውጭ ሀገር የገቡ የምግብ ዘይቶችን በመቀላቀልና በራስ እንደተመረተ አድርጎ ንግድ ምልክት በመስጠት በ0.5ና 1 ሊትር ደረጃ የምግብ ዘይት በማሸግ ለገበያ መውጣቱን አመላክተዋል ።
ለጤና ተስማሚነታቸውንም ይሁን ጎጂነታቸውን ለማወቅ ከምግብ ዘይቱ ናሙና ተወስዶ ምርመራ እንደሚካሄድም አረጋግጠዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የዘጠነኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ደረጃው አማረ ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል እየተቀላቀለ የሚሸጥ የምግብ ዘይት እንዳለ ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ሁሉንም የምግብ ዘይቶች ከነበሩበት መጋዘን በማውጣት የማጣራቱ ሂደት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተይዘው እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።
ተቀጥረው ሢሠሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ቢውሉም ባለቤቱ ግን ያልተያዙና እየተፈለጉ መሆናቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ደረጃው አማረ አነስተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m