
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2013 (አብመድ) በአማራ ክልል የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል የ220 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በክልሉ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የማይበገር ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ሥራ የሚያግዝ የ220 ሚሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክት ከነገ ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ለማዘመን የሚያስችል የባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በክልሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ቀድሞ መለየትና አደጋ ከተከሰተ በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ እና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አብርሃም አበበ እንደተናገሩት የአውሮፖ ኅብረት በኢትዮጵያ አራት ክልሎች የአደጋ ስጋትን ለመከላከልና ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው፤ ይህ የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት አደጋ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችል እንደሆነና በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ፕሮጀክቱ ያልተማከለ የአደጋ ሥራ አመራር አደረጃጀትን በማዋቀር የሥራውን ተፈፃሚነት እንደሚከታተልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
