‘‘የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚጠበቅብኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡’’ ባለሃብት አቶ ተመስገን

570

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 12/2013 (አብመድ) በአማራ ክልል የሚገኙ ትምሕርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አብመድ ያነጋገራቸው ባለሃብት አቶ ተመስገን ከፍያለው ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት በሦስት ሚሊዮን ብር ወጭ በክልሉ የመማሪያ ክፍሎችን አስገንብተዋል፡፡

በክልሉ ካሉት ትምሕርት ቤቶች 84 በመቶ ከደረጃ በታች መሆናቸውን ከትምሕርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ አሁን ካለው 16 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታትም ባለሃብቶች እና የልማት ድርጅቶች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ትምሕርት ቤቶችን አስገንብተዋል፤ እያስገነቡም ይገኛሉ፡፡

በትምሕርቱ ዘርፍ ያለውን ችግር በመረዳት የጎላ ሚና እየተጫወቱ ካሉ ባለሃብቶች መካከል አቶ ተመስገን ከፍያለው አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ተመስገን እንደነገሩን በ3 ሚሊዮን ብር ወጭ ለደብረወርቅ ከተማ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምሕርት ቤት አራት ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ ሕንጻ ገንብተዋል፤ ከሰሞኑ ደግሞ በመሸንቲ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምሕርት ቤት ግቢ ውስጥ ለመዋዕለ ሕፃናት የሚሆኑ ሦስት መማሪያ ክፍሎችን አስገንብተዋል፡፡ በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ የዳስ ትምሕርት ቤቶችን ወደ ግንባታ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ባለሃብቱ አስታውቀዋል፡፡ ለአንድ ሀገር መሰረቱ የተማረ የሰው ሃይል በመሆኑ ባለሃብቶች በትምሕርት ቤቶች ግንባታ ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አለማየሁ ሞገስ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በክልሉ በርካታ ትምሕርት ቤቶች በባለሃብቶች ተገንብተዋል፡፡ በደሴ ከተማ አስተዳደር በ26 ሚሊዮን ብር የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የመርጡለማርያም መሰናዶ ትምሕርት ቤት፣ የጎርጎራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ግሽ ዓባይ ቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም፣ በሽንዲ እና በሌሎች አካባቢዎችም ትምሕርት ቤቶች በባለሃብቶች መገንባታቸውን ዳይሬክተሩ በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ባለሃብቶች ባለፉት ወራት በተከሰቱት ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ማኀበሩን እየደገፉ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡

የክልሉን የትምሕርት ቤቶች ደረጃ ካለበት 16 በመቶ ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ፤ ጥቅምት 15/2013 ዓ.ም ደግሞ በጎንደር ከተማ ከባለሃብቶች እና ከልማት ድርጅቶች ጋር ውይይት ይደረጋል፡፡

ባለሃብቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሀገርን አንድነት ለመናድ የሚሰሩ ሁሉ ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።
Next articleየታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጭር የጽሁፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ 3ኛ ዙር ሁለተኛ ተሸላሚ መኪናቸውን ተረክበዋል፡፡