ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ10 ዓመት ዕቅዱን ለባለድርሻ አካላት አስተዋወቀ።

451

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013ዓ.ም (አብመድ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከተባባሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ለሰው ልጆች መርሀ ግብር ጋር በመሆን አዲሱን የከተማ ልማት አጀንዳ በተመለከተ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ምክክር አድርጓል።

“የከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት ቅንጅታዊ አሠራርን በመተግበር ከተፅዕኖ የተላቀቀ እና ዘላቂ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶችን እንዴት ማምጣት ይቻላል?” የምክክሩ ዋና ትኩረት ነው። በዚህ መንገድ የሚገነቡ እና የሚመሩ ከተሞች ሁለንተናዊ እድገታቸውን እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ከተሞች የሰላም፣ የልማት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማዕከልነታቸውንም ለማስተናገድ ድርሻቸው የጎላ ይሆናል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አይሻ ሙሀመድ (ኢንጅነር) በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው የ10 ዓመት የከተማ ልማት እቅድ አጋር አካላት እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አመሥግነዋል። በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ተከትሎ የሕዝብ ቁጥር እያደገ እንደሆነና ከተሞችም እየሰፉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

እድገቱን ጤናማ አድርጎ ለመምራት ከተሞች የልማት እቅዱን ተከትለው እንዲያድጉ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በጥሩ ጅምር ላይ መሆናቸውንም ሚንስትሯ ጠቁመዋል። በኢትዮጰያ ከ2013 እስከ 2022ዓ.ም የሚተገበር የ10 ዓመት አገር አቀፍ የኮንስትራክሽንና የኢንዱስትሪ መሪ የልማት እቅድ በማዘጋጀት እየተሠራ ባለው ሥራ አጋር የልማት አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ እቅዱን ለማስፈጸም ሚናው የጎላ መሆኑንም ኢንጅነር አይሻ አንስተዋል።

በዓለማቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የከተማ ልማት ፕሮግራሙን በተያዘለት እቅድ ለማስፈጸም ክፍተት መፍጠሩን ያነሱት ሚኒስትሯ ለኑሮ የተመቹ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የማያስከትሉ፣ ዓለማቀፍ የከተማ ልማት መለኪያዎችን ያማከሉ ከተሞችን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መርሀ ግብሩ ተወዳዳሪና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞችን በመፍጠር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑንም ኢንጅነር አይሻ ገልጸዋል። “በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራ ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ አጋር አካላት በኢትዮጵያ በኩል የተያዘውን የ10 ዓመት እቅድ ለማስተዋወቅና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲኖር ለማደረረግ ሥራዎች ተናበው እንዲከናወኑ መረጃ ለመለዋወጥ፣ የመንግሥትን የመሪነት ሚና ለማሳየት፣ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ እና የትኛው ከተማ ላይ መንግሥት ምን ለመሥራት አቅዷል” የሚለውን ለማሳወቅ መድረኩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። በመንግሥት በኩል ዘጠኝ የከተማ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ የገቡ መሆኑ ተጠቁሞ ከነዚህ መካከል ስድስቱ አዲስ ናቸው ተብላል። በተለይ ደግሞ የመሬት ፕላን አንዲሁም የሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፤ ለዚህ ስኬት የአጋር አካላት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከተሞች ኤጀንሲ የመጠለያ ለሰው ልጆች መርሀ ግብር የኢትዮጵያ ኃላፊ አክሊሉ ፍቅረሥላሴ ከተሜነት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋና እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ በተበታታነ መልኩ በከተማ ልማት ሥራ ላይ የተሠማሩ ከ50 በላይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአንድ በመሰብሰብ የፕሮግራሙን እቅድ የጋራ ለማድረግ እና የሀብት ብክነትን በመቀነስ በኩል የተናበበ ሥራ ለመሥራት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የጋራ ሴክሬታሪያት መቋቋሙን አንስተው በዚህ መድረክም ሁሉም አካላት በከተማ ልማት ፕሮግራማቸው ለመሥራት ያቀዳቸውን እቅዶች የጋራ በማድረግ ወደ ሥራ ይገባልም ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ለሰው ልጆች መርሀ ግብር ብር ተወካይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የ10 ዓመት ሀገር አቀፍ የዘርፉ መሪ የልማት እቅድን ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። የከተሞች የአረንጋዴ ልማት ሥራ፣ የአቅም ግንባታ፣ የከተማ አመራር ስልጠና፣ የሰፈራ መርሀ ግብር፣ የተፈጥሮ አደጋን ቀድሞ የመከላከል ሥራን መደገፍ እና ሌሎች ከከተማ ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም የሀገሪቱን የ10 ዓመት የልማት እቅድ ለመደገፍ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ የከተሞች መስፋፋትና የብሔራዊ ልማት ዕቅድ ትግበራ፣ የከተሞች መስፋፋትና ብሔራዊ የልማት ዕቅድ ትግበራ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል ሀገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮን መወጣት እንደሚገባ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አብረሃም በላይ (ዶክተር) ገለጹ፡፡
Next articleየሀገርን አንድነት ለመናድ የሚሰሩ ሁሉ ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።