
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013 (አብመድ) ለአፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ባለመስጠትና የተጋረጡ ወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል፣ ሠላምና መረጋጋትን ማስጠበቅና በልማት ሀገርን የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮን መወጣት ይገባል ሲሉ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አብረሃም (ዶክተር) በላይ ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር አብረሃም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት መላው ሕዝብ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴትን በመናድ ሕዝብን ከሕዝብ መነጠል ዋነኛ ሥራቸው አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በመጠበቅና ሴራቸውን በማክሸፍ ለአብሮነቱ ዘብ ሊቆም ይገባል።
በመግለጫቸው እንዳነሱት በሀገሪቱ በተደረገው ለውጥ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚታይና አሳታፊ ለውጥ መጥቷል።
ይህ ያልተዋጠላቸውና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የሚተጉ ኃይሎች አሁንም ሕዝቡን እያዋከቡና እያጋጩ እንደሆነ ዶክተር አብረሃም አብራርተዋል።
በተለይም በስሙ እየተነገደበት ያለው የትግራይ ሕዝብ ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመተባበር ነጻነቱን በብልሃት ማወጅ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
መላው የትግራይ ሕዝብ፣ በውጭ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመሆንና በጥበብና በማስተዋል ነገን በጋራ መገንባት እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ያለንበት የታሪክ ዘመን እጅግ ማስተዋልና የላቀ የሀገር ባለአደራነት የሚጠይቅበት’’ ነው ያሉት ዶክተር አብረሃም፤ “ወቅቱ አፍራሽ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ የመደርመስ ሥራ የሚሰራበት ነው” ብለዋል።
እንደ መግለጫው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ከጥቂት ወራት ወዲህ ያጋጠሟትንና በመታገል ላይ ያለቻቸውን ጉልህ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን የመጋፈጥ ጉዳይ በቡድናዊ ውስን እይታ የፍላጎት መነፅርና፣ በቆሞ ቀር የአመለካከት ችንካር መፍትሔ የሚያገኝ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ከግብታዊነት ቁንፅል አረዳድ ወጥቶ ከፍ ብሎ የማሰብ፣ የህዝብ ፍላጎትንና ገዢ የሕግ ማዕቀፎችን በኃላፊነት አክብሮ የመጓዝ፣ የዚህን ትውልድ ሀገር የማሻገር ፈታኝ ታሪካዊ ተልእኮ በፅናት የመወጣት፣ በዚህም ሀገርን የማረጋጋትና ማስቀጠል ዋና የጊዜውን ሚና መጫወትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ዶክተር አብረሃም እንዳሉት “አፍራሽ ቡድኑ በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና አለመተማመን ማንገስን እንደ ዋና የህልውናና በስልጣን የመቀጠል መርህ አድርጎ በመውሰድ ለረጅም ዘመን ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የኖረውን፣ ሐይማኖት፣ ዘርና ጎሳ ሳይለይ ዳር እስከ ዳር ተዋልዶ ተሳስቦና ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ፣ ሰውሮ ባስቀመጠው የልዩነት ካርድ በመጠቀም ታሪክ ይቅር የማይለው ደባውን በሌላ ማልያ በመጫወት ከሕዝብ የማይሰወር ተፈጥሯዊ የሴራ ፖለቲካውን ያለ ሀፍረት ቀጥሏል” ።
“ህዝባችን ከዚህ የዜሮ ድምር ታሪክ አጥፊ ጨዋታና የሞራል ዝቅታ በላይ ከፍ ብሎ ሴራዎቹን ይበጣጥሳል፤ በመላው የትግራይ ሕዝብና የእውነተኛ የሀገራችን የፌዴራሊዝም ሀይሎችና ታጋዮች የተለመደ አስተዋይነትና ትእግስት በሕጋዊ ርምጃዎችና በሕዝቦች የተባበረ ክንድ መልሱን ያገኛል” ሲሉም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝቦች ጋር በመሰለፍ በተለያየ ጊዜ መንግስት የሚወስዳቸውን የተጠኑ ፖለቲካዊ እርምጃዎች በመደገፍና ለአፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻቸው ጆሮ ባለመስጠት ከፊት የተጋረጡብንን ጉልህ የወቅቱ ስጋቶችን መከላከል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
“የኮሮና ቫይረስ ስርጭትና የአንበጣ መንጋ የሚያደርሰውን ስጋት በመከላከል፣ የህዳሴ ግድባችን የማጠናቀቂያ ሥራ ላይ መረባረብ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሠላምና መረጋጋትን የማስጠበቅ እና የተዘረጉ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ፕሮግራሞችን በንቃት በመደገፍና በመሳተፍ ሀገር የማስቀጠልና የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮአችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ” በማለት ዶክተር አብረሃም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
