በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ክልል ተወካዮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አሳሰቡ፡፡

518

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013 (አብመድ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ሕዝብ የወከላቸው የምክር ቤቱ አባላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ባለፉት ሁለት የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ከአንድ ተወካይ በስተቀር ከትግራይ ክልል የተወከሉ የምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በምክር ቤቱ በኩል ተወካዮቹ እንዲገኙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ባለመገኘታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡

አፈ ጉባኤው በመግለጫቸው እንዳሉት ማንኛውንም ችግር በውይይት፣ በሕግና አሰራር መፍታት እንጂ ሀገርን የማፍረስና ሕግን የመተላለፍ ተግባር መፈጸም የለበትም።
ዘንድሮ የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ90 በመቶ በላይ የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦቱን ማጠናቀቁን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በምርጫ ሂደቱ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከለውጡ ጋር የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት እየሰራ መሆኑንም አፈ ጉባኤው አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ ወደ ሕዝቡ ይበልጥ በመቅረብ እየሰራ እንደሆነ የጠቀሱት አፈ ጉባኤው፤ በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በገንዘብና ቁሳቁስ 40 ሚሊዮን ብር መለገሱን አስታውሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ የሚገመግሙ የምክር ቤት አባላት ልኡክ ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መንቀሳቀሱንም ገልጸዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የሆቴል ኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ፡፡
Next articleወቅታዊ ስጋቶችን በመከላከል ሀገር የማሻገር ትውልዳዊ ተልዕኮን መወጣት እንደሚገባ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አብረሃም በላይ (ዶክተር) ገለጹ፡፡