በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የሆቴል ኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ፡፡

351

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013 (አብመድ) የሆቴል ኢንቨስትመንት ግንባታዎቹ ሲጠናቀቁ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም ባለፈ ሠፊ የሥራ እድል እንደሚፈጥር የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ መዳረሻና የደረቅ ወደብ ማዕከል የሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ ገና እንደሚቀራት ችግሮች ሲነሱባት ቆይቷል፡፡
ከተማዋ ካላት ፈጣን እድገትና የኢንቨስትመን ፍሰት አንጻር በጥራትም በብዛትም የሚመጥኑ ሆቴሎች እጥረት እንዳለ ዘግበንም ነበር፡፡ በቂ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እጥረት በመኖሩ በተለያየ ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለቀናት አቆይቶ መያዝ አለመቻሉን ነዋሪዎችን፣ ባለሀብቶችን እና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት አነጋግረን ነበር፡፡

ከወራት በኋላ ይህ ጉልህ የከተማዋ ችግር የት ደረሰ ብለናል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓባይነው አበባው በኮምቦልቻ ከተማ 44 ሆቴሎችን ለመገንባት ለባለሀብቶች ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ 10 የሚሆኑት ሆቴሎች በትግባራ፣ 25 የሚሆኑት በቅደመ ትግበራ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ፈቃድ ያገኙት ባለሀብቶች 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዳስመዘገቡም ነው ኃላፊው የነገሩን፡፡ ሁሉም ወደ ሥራ ሲገቡ በዘርፉ ያለውን ችግር ይቀርፋሉ፤ ለ6 ሺህ 555 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የክልሉ መንግሥት በሰጠው ፈቃድ መሠረት በባለፈው ነሐሴ ወር ባለአራትና ባለአምስት ኮኮብ ደረጃ ሆቴሎችን ለሚገነቡ ባለሀብቶች የመሥሪያ ቦታ መሰጠቱን አቶ ዓባይነው አበባው ተናግረዋል፡፡

ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ ከተማ መሆኗን ያነሱት ኃላፊው በሆቴል አገልግሎት ዘርፉም የተሻለ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሬት አቅርቦት በኩል የነበሩ ችግሮች ተፈትተው በምደባ ለባለሀብቶቹ እየተሰጠ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በከተማዋ በሆቴል ቱሪዝምና በሪል ስቴት ግንባታ ዘርፍ ለመሰማራት የተሻለ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን አቶ ዓባይነው አበባው ጠቅሰዋል፡፡ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ሥልት መንደፋቸውንም አስተውቀዋል፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ቶሎ ወደ ሥራ የማይቡ ባለሀብቶችን ክትትል እያደረገ መሆኑንም ኃላፊው አንስተዋል፡፡ “አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን በመደገፍና ክፍተት ያለባቸውን ድግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል” ነው ያሉት፡፡

የሚገነቡ ሆቴሎች ጥራት ከመሃንዲስ፣ ከሕንጻ ሹም እና ከባሕልና ቱሪዝም በተውጣጡ ባለሙያዎች ክትትል እንደሚደረግባቸውም ተናግረዋል፡፡ የሆቴል ቱሪዝም መስፋፋት ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም በላይ ለከተማዋ እድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አቶ ዓባይነው አበባው ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርኩን ጨምሮ 200 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ዓባይነው አበባው መረጃ 34 የሚሆኑት ምርት ጀምረዋል፤ 24 የሚሆኑት ግንባታ አጠናቅቀዋል፤ ሌሎቹ በሂደት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ከተማዋ ለወደብ ቅርብ መሆን፣ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ያለባት መሆኑና የአካባቢው ማኅበረሰብ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ እንድትሆን እንዳደረጋትም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ኮምቦልቻ ከተማ የአውሮፕላን ማረፊያ ያላት መሆን፣ የደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጫ ባለቤትና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዝርጋታ ያላት መሆኗም ሌላኛው ተመራጭ የሚያደርጋት ጉዳይ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው።
Next articleበሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ክልል ተወካዮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አሳሰቡ፡፡