
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የጆርጂያዋን አትላንታ ከሰሜን ወሎዋ ወልድያ አልማ ያስተሳሰራቸው የአብራክ ክፋይ ልጆች ትብብር፡፡ ዛሬ ዛሬ አብዝቶ የማይዘመርለት እና የማይበረክተው ደግ ነገር ነውና ስለደግ ነገር እስኪ ትንሽ እናውጋ፡፡ “ጋን በጠጠር ይደገፋል” እንዳለ የእኛ ሰው።
“የጁ የእግዜር መሃል እጁ” እንዳላት ባለቅኔው እኔም እግር ጥሎኝ የጁ ምድር ላይ ነኝ፡፡ ወልድያ የጥንታዊቷ የየጁ አውራጃ መናገሻ ነበረች፤ ወሎ ጠቅላይ ግዛት መዲናውን ከጦሳ ተራራዋ ስር፣ የፍቅር ንግስት ከሆነችው ከተማ ደሴ ላይ አድርጎ ከአፋር እስከ ጎንደር፣ ከሽዋ እስከ ትግሬ፣ ከአዋሽ እስከ ዓባይ፣ ከበሽሎ እስከ ጃማ የተዘረጋ ታሪካዊ፣ ጥንታዊ እና ህብር የሆነ ጠቅላይ ግዛት ነበር፡፡
ወሎ እና ወሎየነት እነዚህንም አልፎ እስከ አሰብ ድረስ የተዘረጋበት የታሪክ ወቅት እንደነበር ይነገራል፡፡ ወሎ በየዘመናቱ ብቅ ባሉ መንግስታት በርካታ ጊዜ የወሰን እና የአስተዳደር ቅርፅ ለውጥን አስተናግዷል።
ምንም እንኳን በወሎየነቱ ላይ ቅንጣት የስነ ልቦና ለውጥ ባያመጣም፡፡ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ከነበሩት 12 አውራጃዎች አንዱ የጁ ነበር፡፡
ከአዘቦ እስከ ላስታ፣ ከራያ እስከ ዋግ ዱካው ለሚያርፈው ወሎ እምብርቱ የጁ ነው፡፡
“የአሁኒቷን ኢትዮጵያን የሰሯት ወሎየዎች ናቸውና ልታመሰግኗቸው ይገባል” ብለዋል የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕልና አወቃቀርን በስፋት ያጠኑት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቨን የታላቋ ኢትዮጵያ መጽሐፍ ደራሲ። የወሎ አካል የጁ በሀገረ መንግስት ግንባታ ከወንድም ሕዝቦቹ ጋር ምሰሶና ማገር ሆኖ ሀገር ያቀና አውራጃ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡
የጁ ብሎ ወሎ፣ ወሎ ብሎ አማራ፣ አማራ ብሎ ኢትዮጵያ ሳይበልጥ እና ሳያንስ የተንሰላሰለ ኢትዮጵያዊነት በዚህ ግድም ትናንት ነበር፤ ዛሬም አለ፤ ነገም ይኖራል፡፡
የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት ስልጣኔ፣ የዋድላ ቅኔ፣ የሸህ ሁሴን ጅብሪል አስተምህሮ፣ የመምህር አካለ ወልድ ተሞክሮን፣ ለቃኘው የጁ ትምህርት ማለት ምን እንደሆነ በቀላሉ ይገባዋል፡፡
“ፍትህ ዘምበል አለ፣ ትምህርት ተጓደለ” ሲሉት የጎደለውን ለመሙላት፣ ዘምበል ያለውን ለማቅናት አይሰስትም፡፡ ዛሬም የሆነው እሱ ነው፡፡
ቀድሞ ተምሮ ብዙ ላስተማረ ማኅበረሰብ ከትምህርት ደረጃ እና ጥራት መጓደል በላይ የሚያሳስበው ነገር የለም፡፡
በአማራ ክልል ላለፉት ዓመታት ጥያቄ ከሚነሳባቸው ውስንነቶች መካከል ግንባር ቀደሙ የትምህርት ጥራት እና የትምህርት ቤቶች ደረጃ መጓደል ጉዳይ ነበር፡፡ በቅርብ የወጡ የሀገሪቱ የትምህርት ደረጃ ልኬት ውጤቶች የሚያመላክቱትም በአማራ ክልል የትምህርት ቤት ደረጃ ዝቅተኛ እንደሆነ ተደጋግሞ ተደምጧል፡፡
የአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፈው ዓመት አዘጋጅቶ እና በጠቅላላ ጉባኤው አፀድቆ ወደ ትግበራ የገባበት የሦስት ዓመታት የለውጥ እና ስትራቴጂክ ዕቅድ ትኩረቱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ቀዳሚው ነው፡፡
ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በሚተገበረው የለውጥ እና ስትራቴጂክ ዕቅድ ከሕዝቡ በሚሰበሰብ 21 ቢሊዮን ብር ገደማ የክልሉን የትምሕርት ደረጃ ወደ 50 በመቶ እንደሚያሳድገው የማኅበሩ ዕቅድ ያመላክታል፡፡
በመንግስት ባለቤትነት፣ በሕዝቡ የገንዘብ ምንጭነት እና በአልማ አስተባባሪነት የሚተገበረው ይህ ትልቅ የለውጥ ዕቅድ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በየአካባቢው ከሕዝብ ገንዘብ፣ እውቀት እና ጉልበት ይሰበሰባል፤ መልሶም በየአካባቢው የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ይሻሻልበታል፡፡ ከዚህ የተረፈውን ጉድለት ደግሞ እስከ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ነባራዊ እውነታውን ማሳየትና የለውጥ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ማንቃት የአልማ ማስፈፀሚያ ስልት ተደርጎም ተቀምጧል፡፡
በወልድያ ከተማ የተጀመረው የትምህርት ቤት ግንባታም የዚህ ማስፈፀሚያ ስልት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በወቅቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የአልማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የአልማን የለውጥ ዕቅድ ለደጋፊዎቹ ለማስተዋወቅ ወደ ውጭ ሃገራት አቅንተው ነበር፡፡
የአልማን የለውጥ እቅድ የሰሙት ደጋፊዎቹ ሰምተው ዝም አላሉም፤ “በአንድ አካባቢ ሞዴል የሆነ ትምህርት ቤት ገንብተን ለውጡን እንደግፍ” የሚል የመጀመሪያ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በአጭር ጊዜም 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለመሰብሰብ ተንቀሳቀሱና 80 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ተሰብስቦ ከአልማ የሒሳብ ደብተር ውስጥ ደረሰ፡፡
እናም የዚህ ሞዴል ትምህርት ቤት ጅማሮ በወልድያ ተበሰረ፡፡
በጅማሮው ላይ እንዲገኙ ጥሪ የተላለፈላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ከመደበኛው ተሳትፎቸው ሌላ 700 ሺህ ብር ገደማ በሰዓታት ውስጥ ሰበሰቡ፡፡ ከጥሬ ገንዘብ ውጭ እስከ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ድረስ የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ አሽዋ፣ ጠጠር እና ብሉኬት ለማቅረብ በከተማዋ ነዋሪዎች ቃል ተገባ፡፡
ጅማሮው ይህንን ይመስላል፤ ከሃሳብ የተነሳ ተግባር ነውና ነገ ከነገ ወዲያ በደሴ በከሚሴ፣ በማርቆስ፣ በሰቆጣ፣ በደብረ ታቦር፣ በጎንደር፣ በሽዋ፣ በደባርቅና በሌሎች ከተሞች መሰል የትብብር ተግባራትን የምንሰማበትና የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከወታደር እስከ አርሶ አደር፣ ከአስተማሪ እስከ መሪ፣ ከአዛውንት እስከ ወጣት ከተባበርን ለምን ከትናንቱ ከፍታችን ላይ አንደርስም?
ከጆርጂያ እስከ ወልድያ በትብብር የሚገነባውን ሞዴል ትምህርት ቤት ፍፃሜ ለማየት የነገ ሰው ይበለን፡፡
ዘጋቢ: ታዘብ አራጋው ከወልድያ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
