በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሁለት ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ ተከስቷል።

209

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ከሌሊቱ 6:00 ጀምሮ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ወረዳ አንድ ቀበሌ እና ጻግቭጂ ወረዳ አራት ቀበሌዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የግብርና መምሪያው የሰብል ልማት ጥበቃ አስተባባሪ በዛብህ ጌታሁን “የበረሃ አንበጣ መንጋው ከአጎራባች የትግራይ ክልል ወረዳዎች ተነስቶ ትናንት ከሰዓት በኋላ 9:00 አካባቢ ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ጸግቭጂና ሰቆጣ ወረዳ ቀበሌዎች ገብቷል” ብለዋል።

በጻግቭጂ ወረዳ 02፣ 07፣ 08 እና 09 ቀበሌዎች፣ በሰቆጣ ወረዳ ደግሞ 07 ቀበሌ ላይ ተከስቷል።

የአንበጣ መንጋው በጊዚያዊነት በቀበሌዎቹ አረንጓዴ እጽዋት በሚገኙባቸው ተራራማና ደን ቦታዎች ሰፍሮ የእንስሳትን መኖ እያጠፋ መሆኑን አቶ በዛብህ ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋውን መንግሥት ቀድሞ ባሰራጨው ኬሚካልና ባህላዊ የማባረሪያ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከሌሊቱ 6:00 ጀምሮ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የበረሃ አንበጣ መንጋው ወደሰብል እንዳያርፍ የተደረገው ርብርብ ውጤታማ ቢሆንም አሁንም ተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ሊመጣ ስለሚችል ኀብረተሰቡ ሊጠባበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ተጨማሪ ኬሚካልና ግብዓቶችን ክልሉ እየላከ ነው ያሉት አስተባባሪው የአካባቢው መልክአ ምድር አስቸጋሪ በመሆኑ ለመከላከሉ ሥራ ውጤታማነት በተሽከርካሪና ድሮን የታገዘ ርጭት ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበራያ ቆቦ ወረዳ አንበጣን ከመከላከል ጎን ለጎን የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ላይ እየተሰራ ነው፡፡
Next articleየጆርጂያዋ አትላንታ እና የሰሜን ወሎዋ ወልድያ፡ የሁለት ከተሞች የትብብር ወግ!