
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም (አብመድ) ለእንቦጭ አረም መስፋፋት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ወደ ሐይቁ የሚገቡ በካይ እና ደለል የተሸከሙ ፍሳሾችን ለመከላከል ማኅበረሰቡ በሐይቁ ዙሪያ ቋሚ ተክሎችን መትከል እንዳለበት የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሽ በቀለ (ዶክተር ኢንጅነር) አስገንዝበዋል፡፡
የውኃ አካላት ለሰው ልጆች በሚሰጡት የዕለት ተዕለት ጠቀሜታ እና የሀገራትን ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማረጋገጥ ያላቸውን ድርሻ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ አካባቢያዊ ደኅንነትን በማስጠበቅ ለሰዎች አለኝታም መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ “እነዚህ የውኃ አካላት የሚያስገኙልን ጥቅም በምናደርግላቸው ጥበቃ እና እንክብካቤ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል” ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀ፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት የውኃ አካላቱን በሚገባ መንከባከብ ካልተቻለ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፤ እስከወዲያኛው ሊታጡም ይችላሉ፤ በዚህ ረገድ ጣና ሐይቅም ኅብረተሰቡ ሊደርስለት የሚገባው ትልቁ የዓለም ሀብት እንደሆነ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ “ሕዳሴ ግድብን ያለ ዓባይ፣ ዓባይን ደግሞ ያለ ጣና ሐይቅ ማሰብ አይቻልም” ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችውን የጣና ሐይቅ በመንከባከብ እና ወደ ቀደመው ተፈጥሯዊ ገፅታው ለመመለስ ለእንቦጭ አረም መከሰት እና መስፋፋት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ወደ ሐይቁ የሚገቡ በካይ እና ደለል የተሸከሙ ፍሳሾችን መከላከል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በእነዚህ ፍሳሾች አማካኝነት ወደ ሐይቁ የሚገቡ ንጥረ ነገሮች ለእንቦጭ አረም በምግብነት ስለሚያገለግሉ በቀላሉ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሐይቁን ዳርቻዎች ከወቅታዊ አዝዕርት ይልቅ በቋሚ ተክሎች እና ፍራፍሬዎች መሸፈን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡
ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እንዳሉት መሪዎች ኅብረተሰቡን ስለችግሩ ስፋት ማስገንዘብ አለባቸው፤ በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በቱሪዝም፣ በዓሳ ምርት፣ በቡና እና ሌሎች ተክሎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
