
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) የራያ ቆቦ ወረዳ በመስኖ የሚለማ ሰፊ መሬት፣ ለመስኖ እርሻ ከ64 በላይ የተጀመሩ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችና ከ200 በላይ በቆቦ ጌራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶች ይገኛሉ፡፡ በአንበጣ መንጋ የተጎዳውን የሰብል ምርት ለማካካስ የወረዳውን የመስኖ አቅም ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንደሚገባም የወረዳ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
በራያ ቆቦ ወረዳ የበረሃ አንበጣ መንጋ በመጀመሪያ ከተከሰተባቸው ስምንት ቀበሌዎች መካከል አንዷ በሆነችው 05 አዲስ ቅኝ ቀበሌ ተገኝተናል፡፡ እርቃኑን ከቆመ አገዳ እና ፍሬው ከተሸመጠጠ የጤፍ ማሳ መካከል ወደቆሙ አርሶ አደር ጠጋ ብለናል፤ አቶ መንገሻ ዓለሙ የዘጠኝ ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ በክረምቱ የእርሻ ወቅት ስድስት ጥማድ ጤፍ እና ሰባት ጥማድ በቆሎ ዘርተው እንደነበር አወጉን፡፡ የክረምቱ ዝናብ ምቹ እንደነበር አርሶ አደሩ ነገሩን፤ ሰብል ለመሰብሰብ ወር እንኳን ባልቀረው ጊዜ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ ገለባና አገዳ ብቻ አስታቅፏቸው አልፏል፤ ነገን የሚፈሩት አርሶ አደር መንገሻ በሰዓታት ልዩነት የሚፈጠረውን አያውቁምና ዛሬ ለከብት መኖ የቀራቸውን አገዳ በመሰብሰብ ተጠምደዋል፡፡
“አጥፍቶ ጠፊ በልቶናል” ያሉት አርሶ አደር መንገሻ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ለመከላከል የተደረገው ጥረት አንበጣው ከተከሰተ በኋላ የተጀመረ በመሆኑ ሰብላቸውን መታደግ እንዳልቻለም ተናግረዋል፡፡ “የበረሃ አንበጣ መንጋ በመከላከል ሥራው የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል” ብለዋል፡፡ አሁንም ገበሬ በመሬት ተስፋ አይቆርጥምና ዝናብ ቢመጣ ማሳውን የሚተኩበት ዘር፣ አፋጣኝ ድጋፍ እና ለቀጣይ አንበጣው እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እንዲጀመር ጠይቀዋል፡፡ የመከላከሉ ሥራ ያልተጎዱ ቀበሌዎችና አጎራባች ወረዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራም ጠይቀዋል፡፡
በራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳደር መረጃ መሠረት 45 ቀበሌዎች ያሉት የራያ ቆቦ ወረዳ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በ23 ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል፤ 43 ሺህ 613 ሄክታር የሚታረስ መሬት ያለው ራያ ቆቦ የአፋር አዋሳኝ የሆኑት አምስት ቀበሌዎች ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፤ 10 ቀበሌዎች ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ሰብላቸው ሲጎዳ ቀሪ ስምንት ቀበሌዎች ከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ11 ጊዜ በላይ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል፡፡ ሰፊ የሰው ኃይል በማሰማራት በባህላዊ አማራጭ ለመከላከል ጥረት ተደርጓል፤ ሆኖም ግን ስርጭቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እና አዳዲስ ቀበሌዎችም የአንበጣ መንጋው እየተከሰተባቸው መሆኑን በ03 አዩ ቀበሌ ተመልክተናል፡፡
የተለያዩ አደረጃጀቶች፣ የአጎራባች ቀበሌዎችና ወረዳዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች እና ባለሀብቱ ሳይቀር በመከላከል ሥራው ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ መንገሻ አሸብር ነግረውናል፡፡ መብረር የማይችለውን አንበጣ መቆጣጠር ቢችሉም የእድገት ደረጃውን ጨርሶ ከሌላ ቦታ የመጣውን መንጋ ግን መቋቋም አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ አሁንም ከመከላከሉ ሥራ ጎን ለጎን የደረሰ ሰብል ስብሰባ ላይ ስምሪት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት እና የመንግሥት ሠራተኞች የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ አርሶ አደሩን እያገዙ መሆኑን አቶ መንገሻ ነግረውናል፡፡ በአንበጣ የጠፋውን የአርሶ አደሮች ምርት ለማካካስ ሁነኛ አማራጩ መስኖ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡ ወረዳው በሙሉ አቅሙ በመስኖ እንዲያለማ ከተደረገ ከወረዳው አልፎ በአንበጣ የተጎዳውን አካባቢ መመገብ የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚቻልም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከራያ ቆቦ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
