ለትምሕርት የበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

136

በአሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ ግዛት የሚኖሩ የአልማ አባላት፣ ሕዝቡ እና የወልድያ ከተማ አስተዳደር በጋራ ትብብር የሚያሰሩት የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በወልድያ ተጀመሯል፡፡

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም (አብመድ) በአትላንታ ጆርጅያ በሚኖሩ የአልማ ደጋፊዎች፣ በሕዝቡ እና በወልድያ ከተማ አስተዳደር የጋራ ትብብር የሚሰራው “ሚሊኒየም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ግንባታው ተጀምሯል፡፡ በግንባታው የአጀማመር ሥነ ስርዓት ወቅትም ከወልድያ ከተማ ነዋሪዎች እና ባለድርሻ ተቋማት 700 ሺህ ብር ገደማ ተሰብስቧል፡፡

የአንድ ሀገር ሕዝብ መፃዒ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በትምሕርት ነው፡፡ በትምሕርት ላይ የተሻለ እሴት የጨመሩ ሃገራት ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ለውጥ እና ዕድገት ለሌሎች አስተማሪ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን በትምሕርት ላይ የፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ ገና አለመጀመሩን የሚያመላክት ነው፡፡

በአማራ ክልል የሚስተዋለውም ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ያነሰ እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡ ከአልማ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከትምሕርት ቤቶች ደረጃ ማስጠበቅ አንፃር የተለያዩ የመለኪያ መስፈርቶችን በመጠቀም ልኬታው ሲሰራ አሁናዊ ውጤቱ ከ16 በመቶ ፈቀቅ ያለ አይደለም፤ ይህንን መሰረታዊ የትምሕርት ችግር ለመቅረፍ እና ተማሪዎች ብቁና ሀገራዊ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል አልማ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የሚያደረግበት የሦስት ዓመት የለውጥ እና ስትራቴጂ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

አልማ በስትራቴጂክ እቅዱ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት አሁን ያለውን 16 በመቶ አፈፃፀም ወደ 50 በመቶ ለማድረስ አልሞ እየሰራ ነው፡፡ እቅዱን ለማስተዋወቅም ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ተንቀሳቅሶ ሰርቷል፡፡ የዚሁ የአልማ የሦስት ዓመታት የለውጥ እና ስትራቴጂ እቅድ ትውውቅ አካል የሆነው በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ የአልማ ደጋፊዎች፣ ሕዝቡ እና የወልድያ ከተማ አስተዳደር በጋራ የሚያስገነቡት ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል፡፡

በ1 ሺህ 500 ካሬ ላይ የሚያርፈው 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 12 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጭ እንደሚደረግበት የሰሜን ወሎ ዞን እና አካባቢው አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ካሳሁን አምባዬ ገልፀዋል፡፡
ለትምህርት ቤት ግንባታው በአትላንታ ጆርጂያ የሚኖሩ የአልማ ደጋፊዎች 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጭ እንደሚያደርጉ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ እስከሁን 80 ሺህ ዶላሩ ገቢ መደረጉን እና ቀሪው በቅርብ ጊዜ ገቢ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ከከተማዋ ነዋሪ እና ከከተማ አስተዳደሩ የሚሰበሰበው ገንዘብም በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተሰበሰበ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የአልማ የሦስት ዓመታት የለውጥ እና ስትራቴጂ እቅድ በመንግስት ባለቤትነት፣ በሕዝቡ የገንዘብ ምንጭነት እና በአልማ አስተባባሪነት ወደ ውጤት ለመቀየር እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
ትምህርት ቤቱን በፍጥነት ፍፃሜ ላይ ለማድረስ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሀመድ ያሲን ናቸው፤ ድጋፍ ላደረጉ ወገኖች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወልደ ትንሳኤ መኮንን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ የመንግሰት የሥራ ኃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደትም 700 ሺህ ብር ገደማ ተሰብስቧል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከወልድያ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት መማር ጀመሩ።
Next articleፕሬዝዳንት ትራምፕ ሱዳንን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ሊያስወጡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡