
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የ12ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት መስጠት መጀመሩን መምሪያው አስታውቋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ለ12ኛ እና ለ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተና ከመወስዳቸው በፊት ለ45 ቀናት የሚቆይ የማካካሻ ትምህርት ከጥቅምት 09/2013 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ መላክ ጀመረ ተናግረዋል፡፡
“ዛሬ ተቀብለን ማስተማር የጀመርነው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የተጠቀሙ ተማሪዎችን ብቻ ነው፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር የተላከው ጭምብል እስከዛሬ ባይደርሰንም ወላጆች ለልጆቻቸው በገዙት ተጠቅመን ነው ማስተማር የጀመርነው” ብለዋል አቶ መላክ። መማርም ሆነ ማስተማር የሚቻለው ጤና ሲኖር ብቻ ስለሆነ ተማሪዎች ያለማንም ክትትል ጭምብል እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት ከ1ኛ ክፍል በስተቀር ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሦስት ሳምንታት የማካካሻ ትምህርት እንደሚወስዱ የተናገሩት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ከማካካሻው ትምህርት በኋላ የ2013 ትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአንድ እስከ ሦስት ፈረቃ እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ በአንድ እና ሁለት ፈረቃ ብቻ ማስተማር እንደሚቀጥሉ አቶ መላክ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
