
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ)
በአማራ ክልል ነባር የመስኖ ፕሮጄክቶችን ደረጃ የሚገመግምና አዳዲስ ፕሮጄክቶች በምን መልኩ ይሠሩ የሚል ውይይት በባሕር ዳር ተካሂዷል።
ውይይቱ የተደረገው በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶክተር) እና በአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድር ምክር ቤት አባላት መካከል ነው። በክልሉ ርብ፣ መገጭና መገጭ ሰራባ ለርጅም ጊዜ ሲጓተቱ የቆዩ ነባር ፕሮጄክቶች ናቸው።
በውይይቱ በፕሮጄክቶቹ ላይ የሚስታዋለው የትኩረት ማነስ ግድቦቹ በተባለላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አድረጓቸዋል ተብሏል። ለአብነትም መገጭ ግድብ 14 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ተነስቷል።
ርብ ላይ የወሰን ማስከበር ችግር እንዳለ በፌዴራል መንግሥት የሚነሳው ልክ አለመሆኑም በክልሉ በኩል ተመላክቷል። የወሰን ማስከበሩ በ2011 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል ተብሏል።
የፌዴራል ተቋሙ ተቋራጩን በማባበል እንደያዘውም በውይይቱ ተነስቷል። “ተቋራጩንና አማካሪውን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጠበቅ አድርጎ መቆጣጠር አለበት፤ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን መጓተቱ አሁንም ይቀጥላል” ነው የተባለው። በየዓመቱ ፕሮጄክቶቹን የሚያጓትቱ ችግሮች ይነሳሉ፤ ነገር ግን መፍትሔ ላይ ሲሠራ እንደማይታይም ተነስቷል።
ለአርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ በወቅቱ አለመክፈል ችግር መሆኑም ተመላክቷል። በተለይ ርብ ላይ 9 ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ውዝፍ እዳ መኖሩም ተገልጿል። የአርሶ አደሮችን ካሳ መክፈል ግዴታ መሆኑም ተነስቷል።
“የርብ ግድብ ውኃ ቁጥጥር በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በአግባቡ መተዳደር መቻል አለበት፤ የግድቡ ውኃ ያለ አግባብ መለቀቅም ሊታሰብበት ይገባል፣ አርሶ አደሮች በየዓመቱ መቸገር የለባቸውም” ተብሏል።
የካናል አሠራሩም ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል። በተለይም የፎገራ የጎርፍ ጉዳይ በጥንቃቄና በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተመላክቷል።
“በርብ ፕሮጀክት ቀሪ ሥራዎችን ለማጣናቀቅ ታቅዶ የተሠራው 0 ነጥብ 35 በመቶ ብቻ ነው” ተብሏል። የመገጭ ግድብም ባለፈው ዓመት 68 ነጥብ 4 በመቶ ደርሶ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የተሠራው ግን 2 ነጥብ 48 በመቶ ብቻ መሆኑ ነው የተነሳው። ግድቡን በ2013 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙም በውይይቱ ተመላክቷል። መገጭ ሰራባ ላይ የሚታዬው የኃይል አቅርቦት ችግር መፈታት እንዳለበትም ተመላክቷል።
“ነባሮችን ለመጨረስና አዲሶችን ለማስቀጠል ማን ምን ይሥራ?” የሚለው መለየት እንዳለበትም ተነስቷል። በአማራ ክልል አዲስ 7 ሺህ ሄክታር መሬት ያለማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አጅማ ጫጫ አዲስ ፕሮጄክትም ሥራ ተጀምሯል።
“10 ሺህ 980 ሄክታር መሬት ያለማል የተባለለት መገጭ መስኖ ፕሮጄክትም ዘንድሮ ይጀምራል” ነው የተባለው። 9 ሺህ 980 ሄክታር መሬት የሚያለማ የግልገል ዓባይ የመስኖ ልማት ፕሮጄክትም በዚህ ዓመት ይጀመራል ነው የተባለው።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) “ወደ ውስጥ መመለክት ካልቻልን ችግሮቻችን መፍታት አንችልም፣ የቅንጅት ችግር አለብን፣ የፕሮጄክት አመራር ስልቱ ብልሹነት አለበት” ነው ያሉት። ከመሬትና መሬት ጋር ተያይዥ የሆኑ ችግሮችን የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት እንደሚወስድም ገልጸዋል።
ሕግና ሥርዓትን የተላለፉትንም ለፍትሕ ማቅረብ እንደሚጀመር አስታውቀዋል። “የክልሉን ኃላፊነት ለማንም አሳልፈን አንሰጥም” ነው ያሉት። የፌዴራል መንግሥትም የተቋራጭን ጉዳይ ማስተካከል፣ ለክልሉ ሥራዎችን ቆጥሮ መስጠትና ቆጥሮ መረከብ እንዳለበት አሳስበዋል።
“በክልሉ የመሠረተ ልማት ችግር የሆኑትም እየተቆጠሩ ይሰጡ። በፕሮጄክቶቹ መወቃቀስ ማቆም አለብን፣ ‘የማን ኃላፊነት ነው?’ የሚለውን ቆጥረን ርክክብ ማድረግና ሥራዎቻችን በየጊዜው መገምገም አለብን” ብለዋል ዶክተር ፋንታ።
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ “የመገጭ ግድብ ወዲህ ወዲያ ሳይል ማለቅ መቻል አለበት” ብለዋል። “በፕሮጀክቶቹ ላይ የበጀት ችግር የለብንም፣ ችግሩ አሠራሩ ላይ ነው” ብለዋል። ባለፈው ዓመት ያላለቁ ፕሮጄክቶች ላይ ዘንድሮ መንግሥት ግፊት ያደርጋል ነው ያሉት።
በክልሉ 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት ይችላል፣ እያለማ ያለው ግን 368 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑም ተመላክቷል። ክልሉ በርካታ የመስኖ አማራጮች እንዳሉትም በውይይቱ ተነስቷል። በክልሉ በጥናት ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጄክቶች መኖራቸውም ተመላክቷል። ሽንፋ፣ አንገረብና ጀማ በጥናት ላይ ያሉ ናቸው።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
