
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አባላት የ2012 የእቅድ አፈጣጸም እና የ2013 የማኅበሩ እቅድ ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አበባ እሸቴ ለአብመድ እንደተናገሩት በ2012 በጀት ዓመት የአዲስ አባላቱን ቁጥር ማሳደግ ያቋረጡትን ማሰባሰብ እና በሁሉም የክፍለ ከተማው ወረዳች በተሠራው ሰፊ የንቅናቄ ሥራ 1 ሺህ 600 አዳዲስ አባላትን በማፍራት እና ነባሩን አባል በማስተባበር ለአልማ ድጋፍ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰባቸውብ ተናግረዋል።
አልማ በሕዝብ እንዲመራ ለማድረግ በ63 ቀጣናዎች ንቅናቄ በመሥራት መሠረታዊ አባላትን የማፍራት ሥራ እየተሠራም መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተያዘው ዓመትም በክፍለ ከተማው 3 ሺህ አዳዲስ አባላትን ለማፍራት እየተሠራ ሲሆን ለዚህም ኮሚቴውን የማጠናከር ሥራ፣ አዳዲስ አባላትን የማፍራት የቅንጅት ሥራዎችን ማጠናከር ላይ ሰፊ ሥራ በመሥራት በክፍለ ከተማው ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ምክትል ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
አልማ የቆመው የክልሉን ሕዝብ ለመጥቀም እና አጠቃላይ የክልሉን ሁሉን አቀፍ ልማት ለመደገፍ በመሆኑ ሁሉም የአልማ አባል በመሆን ወገናዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።
ከክልል ውጭ የአልማ አስተባባሪ ደጋረገ ስዩም ምንም እንኳ በአዲስ አበባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ቢኖሩም የአልማ አባል ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው ግን ከ46 ሺህ የማይበልጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህን ለመቀየር እና የአባላቱን ቁጥር ከፍ በማድረግ የክልሉን ልማት በጠንካራ ተሳትፎ መደገፍ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ምንም እንኳ በከተማው ያለው የአማራ ተወላጅ ቁጥርም ከፍተኛ ቢሆንም አልማ በክልሉ ስለሚያከናውነው የልማት ተግባር ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ በአባልነት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው ቁጥር ከዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑንና በቀጣይ በትኩረት እንዲሠራበት ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።
የአልማን የአባላት ቁጥር ማሳደግ ድጋፍ ከማሰባሰብ በላይ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የአልማ የሥራ ኃላፊዎች በመገንዘብ ሰፊ የንቅናቄ ሥራ በመሥራት ሁሉንም የአልማ ቤተሰብ ማድረግ እንደሚ ተሳታፊዎቹ አስታውቀዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ የአልማ አባላት፣ መሪዎች እና ደጋፊዎች በተገኙበት የ2013 ጉባኤያቸውን አድርገዋል።
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን -ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
