
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ ኃይሎችን ለመታገል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
ምርጫ በሂደቱ እንጂ በውጤቱ አይለካም፤ የምርጫ ውጤት የሂደቱ ነጸብራቅ ነው፤ ለዚህም በቂ ጊዜ ወስዶ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይገባል፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ በወቅቱ ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ እንዲራዘም መጠየቁና ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሮናቫይረስን በመከላከል ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ከጤና ሚኒስቴር የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው የተራዘመበት መንገድ ባያስማማቸውም የምርጫው መራዘም አሳማኝ እንደነበር ግን ገልጸዋል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ እንዴት መቆየት እንዳለበት አማራጮች እንደነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ አንስተዋል፡፡ እንዳሉትም የፌዴራል መንግሥቱ የሕገ-መንግሥት ትርጉም የሚለውን አማራጭ ተጠቅሞ በሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት እስከሚያበቃ ምርጫው ተራዝሟል፤ የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት ስልጣንም እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ አቶ ናትናኤል እንዳሉት ኢዜማ ያቀረበው ሐሳብ ድንገተኛና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም፤ በዚህ ጊዜ መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔዎች የመንግሥትን የዕለት ከዕለት ተግባር ብቻ ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ የሚል አማራጭ ነበር፡፡
ይህም የሀገር ደኅንነት እና ሉዐላዊነትን፣ የዜጎችን ደኅንነት እና ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን በማድረግ ላይ እንዲያተኩር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን የተላለፈው ውሳኔ ካሉት አማራጮች ሁሉ የተሻለ ነው ብሎ ባያምንም ፓርቲያቸው የመንግሥትን ውሳኔ እንደሚያከብር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴኅ) ሊቀ መንበር ገበሩ በርሄም ምርጫው ሲራዘም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ መሆን እንደነበረባቸው ጠቅሰዋል፤ ነገር ግን ኢዴኅ ዓለም አቀፉን ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ መከላከል እንደሚገባ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡ ሂደቱ በዚህ መልኩ አልፎ ምርጫው እንዲደረግ ቢወሰንም አንዳንዶች ከመስከረም 25፣ አንዳንዶች ደግሞ ከመስከረም 30 በኋላ “መንግሥት የለም” በማለት ሕዝብ እና አንዳንድ የመንግሥት መዋቅሮች ለክልልም ሆነ ለፌዴራል መንግሥታት ተገዢ እንዳይሆኑ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡
አብመድ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅስቀሳው ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ቅስቀሳውን ያደረጉ አካላት መንግሥት የሄደበት መንገድ ችግር አለበት ብለው ቢያስቡ እንኳን አካሄዳቸው ትክክል እንዳልሆነ የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ “መንግሥት የለም” ማለት ሀገር የሚያስተዳድር፣ ሕግ እና ሥርዓት የሚያስከብር አካል የለም እንደማለት ነው፡፡ ተቀባይነት የለውም እንጂ ቅስቀሳው ወደ ለየለት ብጥብጥና ሥርዓት አልበኝነት እንደሚያስገባም ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር ተስፋሁን ዓለምነህ “የአማራ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‘መንግሥት አለ፤ የለም’ ብሎ አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የለበትም” ብለዋል፡፡ ፓርቲው በተደጋጋሚ የሚያነሳውም መንግሥት የሚጠበቅበትን መንግሥታዊ ተግባር አልተወጣም የሚል ነው፡፡ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን በማንሳትም መንግሥት ግን ይህንን ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ምርጫ ብቻውን ሁሉንም ችግር በዘላቂነተት ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው በመግለጽም አዴኃን የሀገር ሰላምና የኮሮናቫይረስን መከላከል ቅድሚያ እንዲሰጠው እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ሊቀ መንበሩ “እንኳን መንግሥት ሳይኖር ቀርቶ እያለም መንግሥታዊ ተግባሩ በአግባቡ ባለመከናወኑ ክቡር የሆነ የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው” ብለዋል፡፡
ስልጣን ሊያዝ የሚገባው በሕዝብ መሆን እንዳለበት ያነሱት አቶ ተስፋሁን ይህም ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላማዊና ነጻ ምርጫ ሲካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አስተያዬት ሰጪዎቹ እንዳሉት ቅስቀሳው ወደ ሥርዓት አልበኝነትና ግጭት በማምራት ባልተገባ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ጥሪው ምን ዓላማ ይዞ እንደተደረገና ለምን ጥቅም ሊውል እንደነበር ሕዝብ መረዳቱንም አብራርተዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቅስቀሳ የሚያደርጉ ቡድኖች በሀገር ሰላም፣ መረጋጋትና በዜጎች ደኅንነት ላይ አደጋ የመጣል ዓላማ ያላቸው በመሆኑ ደጋፊዎቻቸው፣ አባላቶቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያውያን በንቃት እንዲከታተሉ መክረዋል፡፡ እነዚህ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን ለፖለቲካ ዓላማቸው ለመጠቀም እንደሚጥሩ፣ ግጭቶች እንዲነሱ ቅስቀሳ በማድረግም የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት እንደሚጠቀሙ አቶ ናትናኤል ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት የፀጥታ አካል ግጭት ከመነሳቱ በፊት ሊነሱ የሚችሉባቸውን ቦታዎች እና መንስዔዎችን በመለየት አፋጣኝ የመከላከል ርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል፡፡ ግጭቶች ሲከሰቱም አፋጣኝ ርምጃ ወስደው የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን በመተንበይ የመከላከልና ቶሎ በማስቆም በኩል ክፍተት እንደነበር አንስተዋል፡፡
ሕዝቡም ያለተገባ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሰዎችን እንዲመክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ እንዲሠራም መክረዋል፡፡
የኢዜማው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዳሉት የሲቪክ ማኅበራት በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማቀራረብ የውይይት መድረክ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ የማኅበረሰቡን የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት የመገንባት ሚናቸውንም መወጣት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መሆን እንዳለበት በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስምምነት መኖሩንም አንስተዋል፡፡ ስምምነቱ አባላትና ደጋፊዎቻቸውን የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን መብት እንዲያከብሩ በማስተማር እንዲሁም ለሰላምና መረጋጋት መስፈን የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም በስልጣን ላይ ያለውን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በስምምነቱ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወደ ብጥብጥ የሚያመራ ቅስቀሳ መደረጉን እንደማይቀበሉት ያስታወቁት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ሊቀ መንበሩ ገበሩ በርሄ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲስተካከሉ ከመንግሥት ጋር እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ “በህወኃትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው መካረር ለኢትዮጵያ አይበጅም” በማለትም ሁሉንም ያካተተ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአዴኃን ሊቀ መንበሩ ተስፋሁን ዓለምነህ ባስተላለፉት መልእክት የሚታዩ ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱት በተጠናከረ ትግል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ትግል ለማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎችን በመጋፈጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡ በሕዝቦች መካከል ውዥንብር እንዲፈጠር የሚታትሩ አካላትን ሥርዓት ለማስያዝ መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ነው አቶ ተስፋሁን የተናገሩት፡፡ ነጻ ተቋማትም ተግባራቸውን በነጻነት እንዲያከናውኑ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
