ለጎርጎራ ፕሮጀክት ባለሀብቶች የፕሮጀክት መነሻ ዕቅድ እያቀረቡ ነው፡፡

365

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) ገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት ተሳታፊ ለመሆን ያቀዱ በለሀብቶች ከ80 እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የፕሮጀክት ሐሳብ እያቀረቡ መሆናቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ

ገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት በአገር ደረጃ ሊሠሩ በእቅድ ከተያዙት ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች መካከል ነው፡፡ የቦታውን አመቺነት የተመለኩቱ ከ100 በላይ ባለሀብቶች ጥያቄ ማቅረባቸውን የማከላዊ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ዮሐንስ አማረ ተናግረዋል፡፡

እስከ ዛሬ ከ100 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች ከ80 እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የፕሮጀክት ሐሳብ ይዘው ጥያቄ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት ሐሳብ እያቀረቡ የሚገኙት ባለሀብቶች ደግሞ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው፣ ለአካባቢ፣ ለክልል እና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከት የሚችሉት መሆናቸውን መምሪያ ኃላፊ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ሥራውን ለማስጀመር ከሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች መካከል ባለሀብቶች ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት መንገድ የተመቻቼ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የባንክ አግልግሎት በአካባቢው ስለሌለ ተንቀሳቃሽ ወይም በኤቲኤም የሚሠራ ባንክ አግልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የመብራት ጥያቄ ደግሞ የአካባቢ የማኅበረሰቡ የዘመናት ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረው እና የባለሀብቶችም አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት ደግሞ ለፌዴራል እና ለክልል መንግሥታት በማቅረብ ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡

ከዚህ በፊት መሬት በጨረታና በምደባ ወስደው ለታለመለት ዓላማ ያላዋሉ ከ30 በላይ ባለሀብቶችም መሬቱን ተነጥቀዋል፤ የተሻለ ሐሳብ ይዘው ለሚመጡ ባላሀብቶችም መሬት ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጎርጎራ ሀገራዊ ፕሮጀክት የሚሳፈተፉ ባለሀብቶች የአምራች ኢንዱትሪ፣ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬም፣ የእንስስት እርባታ፣ የዓሳ ሀብት ልማት እና የግብርና ምርቶች ማቀነባበር እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡

ከአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘውን ገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት በጥቅምት ሥራ ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ታናግረዋል፡፡ ከእንጦጦ ፕሮጀክት ልምድ የወሰዱ ባለሀብቶችም ከ100 እስከ 200 የሚሆን የሰው ኃይል ወደ ሥራ ለማስገባት መነሻ እቅድ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኝት ኃላፊ ኃይለኢየሱስ ፍላቴ ደግሞ ገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ከዓለም ከሚገኙት የመስህብ ሀብቶች ተመራጭ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ በጣና ዳር የሚሠሩ መናፈሻዎችም ከሩቅ ምሥራቅና አውሮፓ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የቱሪስቶችን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ መሆናቸውብ ገልጸዋል፡፡ ወደ አማራ ክልል ‘‘በብዛት የሚመጡ ቱሪስቶች የታደጊ ሀገራት ናቸው’’ ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት ሲሠራ ደግሞ ሀብት ያላቸውን ቱሪስቶች ማማለል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡ በገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ በቢሮው የ10 ዓመት መሪ እቅድ ላይ መካተቱንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲኖር የሚተጉ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ገለጹ፡፡
Next articleአልማ በአዲስ አበባ የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡