በሰሜን ወሎ ዞን በተከሰተው የበርሃ አምበጣ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረግ ድጋፍ ህጋዊ የመንግስት አሰራርን ተከትሎ እንደሚካሄድ የዞን አስተዳደሩ አስታውቋል፤ግለሰቦች የድጋፍ ሒሳብ ደብተር በመክፈት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ህጋዊነት እንደሌለውም ተጠቁሟል፡፡

298

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) ካለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ጀምሮ በሰሜን ወሎ ዞን የተከሰተው የበርሃ አምበጣ መንጋ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል፤ በተለይም በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የደረሰው ጉዳት በአርሶ አደሩ የምርት ሽግግር ወቅት የተፈጠረ መሆኑ ፈታኝ አድርጎታል ተብሏል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም በዞኑ ከ286 ሺኅ በላይ አርሶ አደሮች አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ይታመናል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን አራት ወረዳዎች እና 38 ቀበሌዎች ላይ የተከሰተው የበርሃ አምበጣ መንጋ በ31 ሽኅ ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብልን በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ጎድቷል፤በተለይም በራያ ቆቦ፣ በሐብሩ እና በጉባላፍቶ ወረዳዎች ባሉ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የደረሰው ጉዳት አፋጣኝ ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው ተብሏል፡፡ አርሶ አደሩ የቤቱን እና የጎተራውን እህል ጨርሶ ማሳ ላይ ያለውን ሰብል የሚጠቀምበት የሽግግር ወቅት በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ አስገዳጅ መሆኑንም ነው ዞን አስተዳደሩ ያመላከተው፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ተስፋው ባታብል በተለይም ከአብመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡ ይህንም ተከትሎ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለራያ ቆቦ እና ሐብሩ ወረዳዎች 3 ሺኅ ኩንታል የምግብ እህል እያጓጓዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአምበጣ መንጋው ስርጭት ከተገታ በኋላም ያደረሰው ጉዳት እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካላት በጥንቃቄ ተለይቶ ለፌደራል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ይላካል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከመንግስት በተጨማሪ የግለሰቦችም ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው ድጋፉ ግን ህጋዊ የመንግስት አሰራርን ብቻ የተከተለ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የባንክ ሒሳብ ደብተር ከፍቶ ድጋፍ ማሰባሰብ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ሰምተናል፤ ይህ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ በድጋፍ ሰም የከፈተ አንድ የሂሳብ ደብተር ተገኝቶ አስፈላጊው ማጣራት እንዲደረግበት ለሚመለከተው የህግ አካል ተላልፏል ብለዋል ምክትል አስተዳዳሪው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ዞን አስተዳደሩ ድጋፍ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ተናግረው እንደአስፈላጊነቱ ድጋፍ ማሰባሰብ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንደሚዋቀር ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል፤ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖችም ህጋዊ የመንግስት መዋቅርን ብቻ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአምበጣ መንጋውን በመከላከል ሂደት ከመንግስት እና ከአርሶ አደሩ ጎን ተሰልፈው ድጋፍ ላደረጉ ወጣቶች፣ ባለሃብቶች፣ ተቋማት እና የከተማ ነዋሪዎች ምክትል አስተዳዳሪው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከወልዲያ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article‹‹አጀንዳው የኅልውና ጉዳይ ነው፤ አርሶ አደሩን አሁን ካላገዝነው ምግብ አይኖረንም፤ ምግብ ከሌለ ደግሞ መኖር አንችልም፡፡›› የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ደኅንነት መምሪያ
Next articleበባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ23 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ግንባታዎች ተመረቁ።