
‹‹ገበሬው ካላመረተ ምርት ከየትም ወደ ከተማ ሊገባ አይችልም፡፡›› ሸዋ የአማራ ወጣቶች ማኅበር
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) በበርሃ አንበጣ መንጋ እየተሰቃዬ ያለውን አርሶ አደር ለመርዳት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መሳተፍ እንዳለበት የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ደኅንነት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ ክስተቱ በታዬባቸው አካባቢዎች ሥምሪት ወስዶ የበርሃ አንበጣ መንጋን በመከላከልና የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑን የዞኑ ሰላምና ደኅንነት መምሪያ ገልጿል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አበራ መኮንን ‹‹የፀጥታ መዋቅሩ ሰላም ሲጠፋ ሰላም በማስከበር፤ በልማት ጊዜ ደግሞ የልማት ሠራዊት በመሆን ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ያረጋግጣል›› ብለዋል፡፡ የኬሚካል ርጭት በማድረግ፣ የአቅመ ደካሞችንና በአንበጣ መንጋ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ወገኖች ሰብል በመሰብሰብ በማኅበረሰቡ ውስጥ ጥሩ መነቃቃት መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
ሰብል ስብሰባው ከአንበጣ መንጋ ጉዳት ባለፈ ከዝናብ እንደሚታደግም ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንጋው ስርጭት እየጨመረ መሆኑን ነው አቶ አበራ ያስታወቁት፡፡ በተለይም ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ያለው ክስተት ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነና መንግሥት የቻለውን እያደረገ ቢሆንም የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡
የሰው ጉልበት በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ተሳትፎው እንደሚቀጥል በመግለጽም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የ32ኛ ክፍለ ጦር አባላት፣ የክልሉ አድማ ብተና፣ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት ወደቦታው እንደሚሠማሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹አጀንዳው የኅልውና ጉዳይ ነው፤ አርሶ አደሩን አሁን ካላገዝነው ምግብ አይኖረንም፤ ምግብ ከሌለ ደግሞ መኖር አንችልም›› በማለትም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ወቅቱ የሚጠይቀውን ርብርብ እንዲያደርግ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ሸዋ የአማራ ወጣቶች ማኅበር የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙ ከጊዜ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡ መንግሥት የቻለውን እያደረገ መሆኑን የማኅበሩ ሰብሳቢ ተክለጻዲቅ ግርማ ነግሮናል፡፡ ነገር ግን የኬሚካል ርጭቱ ሁኔታው በሚጠይቀው ልክ አለመሆኑን አንስቷል፡፡
የበርሃ አንበጣ መንጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ትርፍ አምራች የሚባሉ ናቸው፡፡ የማኅበሩ ሰብሳቢም ‹‹ገበሬው ካላመረተ ምርት ከየትም ወደ ከተማ ሊገባ አይችልም›› ብሏል፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ከፍል ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ለማድረግ መረባረብ እንዳለበትም ተናግሯል፡፡
የሸዋ የአማራ ወጣቶች ማኅበርም በየወረዳው በጎ ፈቃደኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አስተባብሮ አንበጣውን ለመቆጣጠርና የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብ የድርሻውን እንደሚወጣ ሰብሳቢው ተክለጻዲቅ አስታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
