ታሪክ የማዳንና ታሪክ የመሥራት ዘመቻ፡፡

162

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 07/2013 ዓ.ም (አብመድ) የዓባይ ህልውና፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቅ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት፣ የቅዱሳን ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መገኛ ጣና ሐይቅ፤ ክፉውን ዘመን ያሳለፈ፣ ፍጥረታትን ያተረፈ፣ ዓባይን ያንሳፈፈ ሚስጥራዊ ሐይቅ ነው፡፡ የተከማቸው ውኃ ብቻ አይደለም፤ ዓሳና አዕዋፋት ብቻም አይደለም፡፡ የቀደመውን ዘመን ማውጫ የሚመጣው ዘመን አቅጣጫ መትለሚያ፣ ታሪክ፣ ቅርስና ጥበብን ሁሉ አቅፏል፤ ጣና ሐይቅ፡፡

በኢትዮጵያ የተገነኜ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ጣና ከሕመም ጋር መታገል ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ከሕመሙ የሚያላቅቅ የተለያዩ መድኃኒቶች ቢሞከሩለትም እስካሁን ፈውስ አላገኜም፡፡ ጣናን ከበሽታው ለመፈወስ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የተጠሩበት፣ የሚሳተፉበት፣ ታሪክ አትርፈው የራሳቸውን ታሪክ የሚሠሩበት ዘመቻ ተጠርቷል፡፡ ይህ ዘመቻ በጦር ሜዳውና በተለያዩ ዘመቻዎች በጋራ ዘምተው ኢትዮጵያን ያቀኗትን ኢትዮጵያውያንን የሚዘከርና የሚያስታውስ ነው፡፡ በአባቶችና በእናቶች ዘመን ዘመቻው ለዓድዋ ነበር፤ በጋራ ዘምተው በጋራ ድል አደረጉ፡፡ ለካራ ማራም ዘመቻ ነበር፤ በጋራ ዘምተው አሸነፉ፤ የልጆች ዘመን ዘመቻ ደግሞ ጣናን ማትረፍ ሆኗል፡፡ እንደ አባቶቻቸው በጋራ ከዘመቱ የአባቶች ታሪክ ይደገማል፤ ታሪክም በታሪክ ይደገፋል፤ ጀግንነታቸውም በጣና ገዳማት የታሪክ መዝገብ በክብር ይሰፍራል፡፡ የኅብረትና አንድነት ዘመቻውን ካልደገሙት ግን ይህ ትውልድ አንገቱን ይደፋል፤ የቀደመውም ታሪክ ያድፋል፡፡ ተከታዩም በአባቶቹ ያፍራል፤ ዘመቻው ኢትዮጵያዊነትና ኅበረት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ በኅብረት ከተዘመተ ደግሞ ድሉ አይቀሬ ነው፤ ለዘመቻው ከተሰለፍን ድል መንሳታችን አይቀርም፡፡

ታላቁ ጣና ከ4 ሺህ 300 በላይ ሄክታር የሚሆነው በእምቦጭ ተይዟል፡፡ ‹‹ሕዳሴ ግድብን ያለ ዓባይ፤ ዓባይን ደግሞ ያለ ጣና ማሰብ አይቻለም›› በሚል መሪ ሐሳብ ከጥቅምት 9 እስከ ኅዳር 9 ቀን 2013ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር ያክል የሚቆይ ኢትዮጵያውያን ወደጣና ሐይቅ እንዲዘምቱ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የዘመቻውን ፋይዳ በተመለከተ ከአብመድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጄንሲ የብዝኃ ሕይወት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር መዝገቡ ዳኛው ‘‘በዚህ ዓመት የተደረገው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ጥሩ ነው፤ ዘመቻው የተጠራበት ጊዜም ወቅታዊ ነው’’ ብለዋል፡፡ እምቦጭ ፍሬ ሳያፈራ ዘመቻው መጀመሩ ትልቅ ነገር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ዘመቻው ሀገር አቀፍ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ዘመቻው ከዚህ ቀደሙም የተለዬ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እምቦጭ በስምንት ወረዳዎችና በ30 ቀበሌዎች ላይ መከሰቱን ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ነው፤ ዳይሬክተሩም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ዘመቻው የእምቦጭ አረምን በማስወገድ በኩል የተሻለ አፈጻፀም ሊኖረው እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ ከዘመቻው ጎን ለጎን ሌሎች አማራጮችን የመጠቀሙ ሂደትም አብሮ ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡ በዘመቻው እምቦጭን ከ80 በመቶ በላይ ማስወገድ ይቻላል ተብሎ እቅድ እንደተያዘ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዘመቻው የሚሳተፈው አርሶ አደሩ ወደመኸር ሥራ የሚገባበት ወቅት በመሆኑ እቅዱ እንዳይሳካ ችግር ሊሆን እንደሚችልም ሰግተዋል፡፡ በዘመቻው አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ የሚገኘውን እምቦጭ አረም ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ የሚቻልበት እድል መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ በአረሙ ከተያዙት ቀበሌዎች ከ60 በመቶ (18) በላይ የሚሆኑትን በአንድ ወሩ ዘመቻ ከእምቦጭ ማጽዳት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ቀበሌዎች ግን በስድስት ወር ሥራም ማስወገድ የማይቻልበት እምቦጭ የከፋባቸው መኖራቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ወር በሚቆዬው ዘመቻ በመካከል የበዓላት ቀን ስለሚኖሩ የተፈለገውን ያክል ማሳካት እንዳይቻል እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡ እምቦጭን ከጣና ላይ ለማስወገድ ተጨማሪ ዘመቻዎች እንደሚያስፈልጉም አስገንዝበዋል፡፡

ከክረምቱ መክበድ ጋር ተያይዞ ጣና ሞልቶ በመፍሰሱ ከሐይቁ ሙሉ በሙሉ አረሙን ያወጣባቸው ቀበሌዎች መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ‘‘ይህ መልካም አጋጣሚ ነው’’ ያሉት ዳይሬክተሩ በአርሶ አደሩ ማሳ የወደቀውን የእምቦጭ አረም አርሶ አደሩ በተከታታይ ሥራው ማጥፋት የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራልም ነው ያሉት፡፡ በዘመቻው በአርሶ አደሩ ማሳ ያረፈውንና በሐይቁ ላይ ያለውን የማስወገድ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ አመቺ የሆኑ የማስወገጃ ቦታዎችን በመምረጥ በማከማቸት እንዲደርቅና እንዲቃጠል እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡ ዘመቻው ለቀጣይ የአረም ማስወገድ ሥራውን ቀላል ሊያደርገው እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

አንድ ወር በሚቆዬው ዘመቻ ኤጄንሲው ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ባለቤት እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡ በዘመቻው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት የጤና ቢሮ የራሱን ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ ‘‘እስካሁን ድረስ የቅንጅት ሥራ ችግር ነበረብን’’ ያሉት አቶ መዝገቡ ‘‘ተቀናጅተን መሥራት ካልቻልን ጣናን ልናታደገው አንችልም’’ ነው ያሉት፡፡ ዘመቻው ለቀጣይ ሥራ ተነሳሽነትን ይፈጥራል እንጂ ሙሉ ለሙሉ እምቦጭን ያስወግዳል ማለት እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ሥራው እስከ ሰኔ 30 ድረስ የሚቀጥል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ እምቦጭን ለማስወገድ ያዝ ለቀቅ ሳይሆን ጠያቂና ተጠያቂ ኖሮት መሠራት እንዳለበትም ነው ያመለከቱት፡፡ ዘመቻው አረም ከመንቀል ባለፈ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ፣ ሀገራዊ ሀብት ላይ መደራደር እንደማያስፈልግና አንድነትን ለውጭ ጠላቶቻችን ማሳያ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ‘‘ጣና የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው፣ የቻለ በጉልበቱ፣ ያልቻለ በሐሳብና በዕውቀቱ ድጋፍ ማድረግ መቻል አለበት’’ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ምስል፡- ከድረገጽ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየደባርቅ-ዛሪማ ሊማሊሞ ተለዋጭ መንገድ የት ደረሰ?
Next article‹‹አጀንዳው የኅልውና ጉዳይ ነው፤ አርሶ አደሩን አሁን ካላገዝነው ምግብ አይኖረንም፤ ምግብ ከሌለ ደግሞ መኖር አንችልም፡፡›› የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ደኅንነት መምሪያ